በሀገሪቱ የሠራተኞች ሃብት የማስመዝገብ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው

75

ድሬዳዋ ነሐሴ 4/2012 (ኢዜአ) ሙስናንን ለመከላከል የሚያግዝ የሠራተኞች ሃብት የመመዝገብ ሂደት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፌደራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ስለመዝገባው አፈጻጸም በኮሚሽኑ የድሬደዋ የቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤት የስነምግባር መኮንኖች እና ባለሙያዎች የሁለት ቀናት ስልጠና ተሰጥቷል።

በኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ በተለይ  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሠራተኞች የሃብት ምዝገባው የሚከናወነው በሁሉም ክልሎች እንዲሁም  አዲስ አበባና ድሬዳዋ  አስተዳደሮች  በሚገኙ የኮሚሽኑ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች ነው፡፡

ለየክፍሎቹ ባለሙያዎች ስለሃብት አመዘጋገብ ሥርዓትና ሂደት በተዘጋጁ ቅፆች ላይ ሥልጠና በመስጠት መረጃ የማሰባሰቡ ተግባር በተያዘው  ሳምንት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በሚቀጣይ ደግሞ ሃብት የማስመዝገቡ ሥራ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ 

ቀደም ሲል በተመረጡ የተወሰኑ ሠራተኞች ላይ ብቻ ሲከናወን የነበረው የሃብት ምዝገባ አሁን ግን በሁሉም ደረጃ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ከ1 ሚሊዮን በላይ  የልማትና የመንግስት ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ለዚህም  ሥራውን ለሚከናወኑ ስልጠናና ሌሎችም ዝግጅቶች እየተደረገ ነው።  

እንደ አቶ አክሊሉ ገለጻ፤ የሃብት ምዝገባው የሌብነት ቀዳዳዎችንና የሙስና በሮችን በመዝጋት የፀረ-ሙስና ትግሉን ፍሬያማ ያደርገዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት ኮሚሽኑ ሃብት ከማስመዝገብ ባሻገር የተመዘገበን ሃብት በተገቢው መንገድ የማጣራት ሥራ የሚከናወንና የተጠያቂነት ስርዓትን የሚያሰፍን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኮሚሽኑ ባለሙያዎች መላውን ህዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ ከሙስናና ምዝበራ ነጻ የሆነ ትውልድና ሀገር ለመገንባት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለበቸውም አሳስበዋል፡፡ 

በኮሚሽኑ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክንዱ ጥበቡ በበኩላቸው፤ በአስተዳደሩ ከሰኔ 1 እስከ ሐምሌ 30/2012 ዓ.ም ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ አመራሮች የሃብት ምዝገባ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መመዝገብ ከሚገባቸው 150 የሚሆኑ አመራሮች መካከል 110  ሃብት ማስመዝገባቸውን አመልክተው  በተሰጠው ጊዜ ሃብታቸውን ያላስመዘገቡ " በፌደራል አቃቤ ህግ በኩል በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል "ብለዋል፡፡

የሠራተኞች የሃብት የመመመዝገቡ ሥራ  ግንዛቤ በማስጨበጥ ከ8ሺህ  በላይ ለመመዝገብ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

በድሬዳዋ ለቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤቱ  የስነምግባር መኮንኖች እና ባለሙያዎች ስልጠናውን የሰጠው  የፌደራል ስነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም