የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቀቀ

78

ነሀሴ 3/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ከትናንት ጀምሮ ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቀቀ።

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በሰጡት መግለጫ ፓርቲው በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በስብሰባውም ህወሃት እና ኦነግ ሸኔ ከውጭ ሀይሎች ጋር በመተባበር የታላቁን የኢትዮጵይ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እና በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ከውጭ ሀይሎች ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆኑን ተመልክቷል ያሉት አቶ ፍቃዱ ይህንንም ፓርቲው እንደሚታገለው ገልፀዋል።

ከፍተኛ አመራሩ እና አባላቱ አቋም ይዞ መታገል ላይ ክፍተት እንዳለባቸው መገምገሙንም ጠቅሰዋል።

ሌብነትም እንደ ችግር ተነስቶ አባላቱም ሆነ አመራሩ ተግባሩን እንዲታገሉ አቅጣጫ መቀመጡን ነው ያመለከቱት።

በአመራሩ ውጤት ማስመዝገብ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ላይ ክፍተት እንዳለ መታየቱን ያነሱት አቶ ፍቃዱ በተደረገው ግምገማ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል ሲል ኤፍ.ቢ.ሲ ዘግቧል።

በዚህም መሰረት ሶስት የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶክተር ሚልኪሳ ሚደጋ እና ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታግደዋል ብለዋል።

ይህም ውሳኔ በፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ያመለከቱት።

ፓርቲው የልማት፣ የሰላም እና የለውጥ ስራዎች ላይ አበክሮ እንደሚሰራም አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም