በቤይሩት በተከሰተው ፍንዳታ ተጨማሪ አንድ ኢትዮጵያዊት ሕይወቷ አለፈ

54

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 3/2012 (ኢዜአ) በሊባኖስ መዲና ቤይሩት በቅርቡ በተከሰተው ፍንዳታ ተጨማሪ አንድ ኢትዮጵያዊት ሕይወቷ ማለፉ ተገለጸ። በፍንዳታው ሕይወታቸው አልፎ ማንነታቸውና ዜግነታቸው ያልታወቁ ዜጎች ላይ በተደረገ ማጣራት ኢትዮጵያዊያን እንደማይገኙ ተረጋግጧል ተብሏል።

ከአምስት ቀናት በፊት በቤይሩት ወደብ የደረሰው ከባድ ፍንዳታ የብዙ ዜጎችን ህይወት ሲቀጥፍ ብዙ ንብረት አውድሟል።

በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንሱል ጀነራል አቶ ተመስገን ኡመር በፍንዳታው ምክንያት የአንድ ተጨማሪ ኢትዮጵያዊት ሕይወት ማለፉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ህይወቷ ያለፈው ዜጋ በፍንዳታው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት በጽኑ ህሙማን ክፍል የህክምና እርዳታ ሲደረግላት ቆይታ ትላንት ሕይወቷ ማለፉን ተናግረዋል።

በዚህም በፍንዳታው ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ሁለት መድረሱን ነው ያመለከቱት።

እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ ከዚህ በፊት የሞተው ኢትዮጵያዊ ሕይወቱ ያለፈው ፍንዳታው በተከሰተበት ቅጽበት ነው።

ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ በሞቱት ኢትዮጵያዊያን የተሰማውን ሀዘን ገልጾ ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅና ጓደኞች መጽናናትን ተመኝተል

በአሁኑ ወቅት አንድ ኢትዮጵያዊ በጽኑ ሕክምና ክፍል እንደሚገኝ ገልጸው፤ ቀላልና መካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ሰባት ሰዎች ሕክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በቤይሩት ወደብ በደረሰው ፍንዳታ ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች የ15ቱ አስክሬን ዜግነታቸውንና ማንነታቸው እንደማይታወቅ ነው አቶ ተመስገን የተናገሩት።

ሦስት ቡድኖች በስምንት ሆስፒታሎች በሚገኙት ማንነታቸውና ዜግነታቸው ባልታወቁት 14 ሰዎች ላይ ባደረጉት ማጣራት ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደሌለ መረጋገጡንም አቶ ተመስገን አመልክተዋል።

የተቀረውን አንድ አስክሬን በቀላሉ ለመለየት የሚያስቸግር በመሆኑ የዘረመል (የዲ.ኤን.ኤ) ምርመራ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።

ፍንዳታውን ተከትሎ በሊባኖስ ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን መርዳት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በሊባኖስ ከሚኖሩ ዳያስፖራ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ማህበር አባላት ጋር ትላንት ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል።

"በውይይቱም በፍንዳታው ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች መጠለያ እንዲያገኙና የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል" ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የኢኮኖሚ ቀውሱ እያደረሰ ባለው ጉዳት ዜጎች ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ በዋናነት መግለጻውቸውንም አቶ ተመስገን አንስተዋል።

በምክክሩ ላይ የተነሱ ሀሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱና የኮምዩኒው አባላት በጋራ እንዲሚሰሩና ድጋፍ የሚያሻቸውን ዜጎች የመለየት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት 15 ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ነው የገለጹት።

ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን (ኤም ኤስ ኤፍ) በፍንዳታ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ የሚቻልበትን ስርአት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

"ቆንስላ ጽህፈት ቤቱም ከቡድኑ ጋር በቅርበት በመስራት ለዜጎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያደርጋል" ብለዋል።

በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በደረሰው ከባድ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች ለማጽዳት ፍላጎት እንዳላቸው ጽህፈት ቤቱ መረጃ እንደደረሰውም አቶ ተመስገን ገልጸዋል።

ይህ ተግባር ሰብአዊነት የተሞላበት ቢሆንም ዜጎች በሚያጸዱበት ጊዜ አደጋ ላይ ያሉ ቤቶች ፈርሰው ለተጨማሪ ጉዳት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አሳስበዋል።

የሊባኖስ መንግስት ድጋፍ ያሻኛል ብሎ በይፋ ጥያቄ ሲያቀርብ በተደራጀና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ስራውን ማከናወን እንደሚቻል ነው አቶ ተመስገን ያመለከቱት።

ከፍንዳታው በኋላ መንግስት ላይ የአሰራር ክፍተት አለ በሚል የተቃውሞ ሰልፍ መጀመሩን የጠቆሙት አቶ ተመስገን፣ ሰልፎቹ ወደ ግጭትና ወደ ብጥብጥ እያመሩ መሆኑን ነው የገለጹት።

በመሆኑም በሊባኖስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ሰልፍ ባለባቸው አካባቢዎች እንዳይገኙና በቤታቸው እንዲቆዩ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ጥሪ ማድረጉን አመልክተዋል።

ዜጎቹ ከሊባኖስ መንግስት የሚሰጡ መግለጫዎችን እንዲከታተሉና እንዲተገብሩ መልዕክት መተላለፉንም ጠቁመዋል።

"ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ በቅርበት እየተከታተለ ነው" ብለዋል።

በቤይሩት ወደብ በደረሰው ከባድ ፍንዳታ እስካሁን 158 ሰዎች ሲሞቱ ከስድስት ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

ፍንዳታውን ተከትሎ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሲሆን በሰልፉ በተፈጠረው ግጭት ከ728 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም