የምርምር ማዕከሉ በለቀቃቸው የስንዴና ድንች ዝርያዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ

49

ጎባ ነሐሴ 2/2012 (ኢዜአ) የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር አግኝቶ የለቀቃቸውን የተሻሻሉ የስንዴና ድንች ዝርያዎችን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለጹ።

በምርምር የተለቀቁት ዝሪያዎች ድንቹ “ወቢ” እንዲሁም የስንዴ ዝሪያው ”ሃጫሉ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውና በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ መሆናቸው ተመላክቷል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳሉት ከማዕከሉ በምርምር የሚወጡትን ዝርያዎች መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነትና ተጠቃሚነታቸው እያደገ መጥቷል።

ከማዕከሉ ከሚወጡ ዝርያዎች  ከሚጠቀሙ የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ታጁ አብዱልቃድር  በሰጡት አስተያየት የምርምር ማዕከሉ በየጊዜው የሚያወጣቸውን የሰብልና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከማዕከሉ ጋር ያላቸው ትሥሥርም የጠበቀ መሆኑን አውስተው “ከማዕከሉ የሚለቀቁ ዝርያዎችን መጠቀም ከመጀመራችን በፊት የምናስገባው ስንዴ በሄክታር ከ20 ኩንታል አይዘልም ነበር፤ አሁን ግን እስከ 50 ኩንታል ማምረት ችለናል” ብለዋል።

ማዕከሉ ምርጥ የድንች ዝርያዎችን ማቅረቡ ደግሞ ተጨማሪ ገቢን ከማስገኘት በተጓዳኝ በተለይም የሰብል ማፈራረቅ ሥልት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።

በእጃቸው የሚገኘው የሰብል ዝርያዎች ዝቅተኛ ምርት ከመስጠታቸውም በላይ በበሽታ ስለሚጠቁ የልፋታቸውን ያህል ምርት አግኝተው እንደማያውቁ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር ደረጃ ካሣሁን ናቸው።

አርሶ አደሩ እንዳሉት ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ የምርምር ማዕከሉ ያወጣውን የተለያዩ ዝርያ ከሄክታር እስከ 60 ኩንታል ስንዴ ማምረት ችለዋል።

በማዕከሉ የአትክልትና የቅመማ ቅመም ተመራማሪ አቶ ጌታቸው አሰፋ በበኩላቸው ዝሪያዎቹ ለሰባት ዓመታት በምርምር ሥር የቆዩና ውጤታማነታቸው በብሔራዊ የዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ተገምግመው የተለቀቁ ናቸው ብለዋል።

ዝርያዎቹ በምርታማነታቸውም የተሻሉ ከመሆናቸው በላይ በሽታን መቋቋም መቻላቸውና በተለይም በባሌ ያልተለመደው የሰብል ፈረቃ ዘዴ ፈጥነው ለሌሎች ሰብሎች ማሣ የሚለቀቁ መሆናቸው የተለየ እንደሚያደርጋቸውም አስታውቀዋል።

በምርምር የተለቀቁት ዝርያዎች ድንቹ “ወቢ” እና የስንዴ ዝርያው ደግሞ ”ሃጫሉ ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውና በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ ናቸው።

“ወቢ” የተባለው የድንች ዝርያ በሄክታር 400 ኩንታል ”ሃጫሉ” የተባለው የስንዴ ዝርያ ደግሞ 61 ኩንታል እንደሚሰጥ በምርምር መረጋገጡንም አስረድተዋል።

ማዕከሉ የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናው እንዲረጋገጥ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የምርምር ማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ በሪሶ ናቸው።

ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት በምግብ እህልና እንስሳት መኖ ላይ ትኩረት ያደረጉ ከ78 የሚበልጡ ቴክኖሎጂዎችን ለአምራቹ በማድረስ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አውስተዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ከማዕከሉ በምርምር የወጡ ሁለት የተሸሻሉ የድንችና ስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በስፋት  ለማሰራጨት ከምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን አመልክቷል። 

የሲናና ምርምር ማዕከል በ1978 ዓ.ም ከተቋቋመ ወዲህ የአሁኑን ጨምሮ  በምግብ እህልና በእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ 80 የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም