ወጣቱ የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል ከሚሰሩ አጥፊዎች ሊጠነቀቅ ይገባል-- ወጣቶች

67

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 2/2012 ( ኢዜአ) ወጣቱ በጥቅም በመደለል የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል ለሚሰሩ አጥፊዎች ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳይሆን ሊጠነቀቅ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሞ ወጣቶች ተናገሩ።

በአጥፊዎች በሚለኩሰው እሳት የሚሳተፉ ወጣቶች ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ለሕግ አሳልፎ መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ወጣቶች መካከል ስለሺ ደቻሳ፣ መሳይ ትኩ እና አዲሱ ዑልጋ የኦሮሞ ወጣት ከሌሎች የአገሪቱ ወጣቶች ጋር ታግሎ ለውጥ ቢያመጣም አገራዊ ለውጡን በማደናቀፍ ወደኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

አጥፊዎች በየቦታው እሳት እየለኮሰ ወጣቱ የናፈቀውን ሰላም ለማደፍረስ እየጣሩ መሆኑን ገልጸው፣ የኦሮሞ ወጣት የሚፈልገው ይህን አይደለም ብለዋል። 

ወጣቶቹ በቅርቡ በተከሰተው የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ሰበብ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና ኢትዮጵያን ለማተራመስ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል።

በዚህ የጥፋት ተግባር በንጹሃን ላይ ግድያ መፈጸሙና ንብረት መውደሙ ከኦሮሞ ባህልና እሴት ውጭ መሆኑን ገልጸው፤ ድርጊቱን እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።

በቀደሙት ጊዜያት የኦሮሞ ወጣት ግፍ ይደርስበት እንደነበር የሚናገሩት ወጣቶቹ ይህን ሲፈጽሙ የነበሩ አካላት ለኦሮሞ ተቆርቋሪ መስለው መታየታቸው አስገራሚ ነው ይላሉ።

"ከኦነግ አባላት ጋር የህወሓት ደጋፊዎች በአሜሪካ እና አውሮፓ ለኦሮሞ ተቆርቋሪ መስለው ሰልፍ መውጣታቸው አሳዛኝ ድርጊት ነው" ሲሉም ተችተዋል።

ለኦሮሞ እንታገላለን እያሉ ከህወሓት ጋር የሚሰሩ አካላት ቢኖሩም የኦሮሞ ወጣት ግን ህወሃትን ሊናፍቅ አይችልም ይላሉ።

በመሆኑም ወጣቱ በጥቅም ተደልሎ የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል ለሚሰሩ ድርጅቶች ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ መክረዋል። 

በውጭ አገር ያሉ የኦሮሞ ተወላጆችም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ከሚሰሩ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በአጥፊዎች በሚለኩሰው እሳት የሚሳተፉ ወጣቶች ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ለሕግ አሳልፎ መስጠት ተገቢ መሆኑንም ነው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሞ ወጣቶች ያሰመሩበት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም