ኢትዮጵያዊው የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት አሰልጣኝ የዓለም አቀፉ ቴኳንዶ የአፍሪካ አሰልጣኞች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆነ

67
አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2010 ኢትዮጵያዊው የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት አሰልጣኝ ማስተር አዲሱ ኡርጌሳ የዓለም አቀፉ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የአፍሪካ አሰልጣኞች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ። የአፍሪካ አሰልጣኞች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጡን የሚያሳይ ደብዳቤ ከዓለም አቀፉ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የአፍሪካ ፕሬዚዳንት አህመድ ፋውሊ እንደተላከለት ማስተር አዲሱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል። የ38 ዓመቱ የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኝ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የኮሚቴው ሊቀመንበር ሆነው የሚያገለግሉ ይሆናል። ማስተር አዲሱ የአፍሪካ አሰልጣኞች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ በመመረጡ ምክንያት የዓለም አቀፉ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አሰልጣኞች ኮሚቴ አባል መሆን ችሏል። በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ የወርልድ ቴኳንዶ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን በአስተባባሪነት መምራትና ማሰልጠን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አዳዲስ የአሰልጣኝነት የንድፈ ሀሳብና የተግባር እውቀቶችና ህጎች ካሉ በአህጉሪቷ ለሚገኙ አሰልጣኞች ማስተዋወቅ የሊቀመንበርነቱ ዋነኛ ስራ እንደሆነ ተናግሯል። ማስተር አዲሱ ያገኘው ሹመት በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የረጅም ጊዜያት የልፋት ውጤቱ እንደሆነና በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። በቀጣይ ጊዜያት የአሰልጣኝነት ስራውን በመተው በአመራርነት ላይ በማተኮር በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች በኢትዮጵያ ያለውን የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ለማሳወቅ ጥረት እንደሚያደርግም ነው ማስተር አዲሱ የተናገሩት። በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የስድስተኛ ዳን ማዕረግ ያለው ማስተር አዲሱ ኡርጌሳ ከ20 ዓመት በላይ በስፖርቱ ውስጥ ቆይቷል። የኮሪያውያን የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ብዙ ጥበባዊ ይዘቶችን (ስልቶችን) በውስጡ ያካተተ ስፖርታዊ ክንዋኔ ነው። አዕምሮንና ሰውነትን ማሰልጠን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም