የአማራ ወጣቶች መስዋዕትነት የህወሃትን መራሹን የአፈና ስርዓት ለማስወገድ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው

171

ባህር ዳር (ኢዜአ) ነሐሴ 1/2012 የአማራ ክልል ወጣቶች የከፈሉት መስዋትነት በወቅቱ የነበረውን የአፈና ፖለቲካ ለማስቀየር ያስገደደ መሆኑን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽፈት ቤት ሃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

ነሓሴ 1/2008 ዓ.ም ለአማራ ህዝብ ነጻነት፣ እኩልነትና ፍታዊ ተጠቃሚነት ሲሉ ለተሰዉ የባህር ዳርና አካባቢዋ ወጣቶች የሰማዕታት መታሰቢያ መንገድ ሲሰየም የመታሰቢያ አደባባይ የመሰረት ድንጋይም ዛሬ ተቀምጧል።


በህወሀት የተዛባ የፖለቲካ ስሪት ምክንያት ወጣቱ በአማራው ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረው ጫና እንዲስተካከልና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ስላማዊ ትግል ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።

"ወጣቶቹ ነሃሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ለክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት፣ የአማራ ህዝብ በማይወክሉት መሪዎች መተዳደር የለበትም፣ በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት ይሻሻል፣ የማንነት የወሰን ጉዳዮች እልባት ያግኙ በሚል ጠንካራ አቋም ለመንግስት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል" ብለዋል። 

"ጥያቄዎቹ ጥቅሙን እንደሚነኩት የተገነዘበው በወቅቱ ሀገሪቱን በበላይነት ሲመራ የነበረው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በወጣቶቹ ላይ ግፍ የተሞላበት እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል" ብለዋል።

ወጣቶቹን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመሩ በመገፋፋትም ከ40 የሚበልጡት አሰቃቂ የህይወት መስዋትነት ሲከፍሉ በበርካቶች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉን ተናግረዋል።

"የወጣቶቹ መስዋትነት አፋኙ ሕወሃት መራሽ ሥርዓት ላይመለስ እንዲፈራርስ መነሻ የነበረ ቢሆንም አሁንም ወጣቶቹ ዋጋ የከፈሉባቸው የአማራ ህዝበ ጥያቄዎች አልተመለሱም"ብለዋል።

ከጥያቄዎቹ መካከል የሕገ-መንግስቱ መሸሻልና የወልቃይትና የራያ የወስንና የማንነት ጥያቄዎች እስካሁን እንዳልተመለሱ ጠቅሰው፤ "የክልሉ መንግስት ጉዳዩ በህግ አግባብ እንዲመለስ በትኩረት እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ሐምሌ 5 ፣ 24 እና ነሃሴ 1/ 2008 ዓ.ም የአማራ ወጣቶች ለክልሉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ መሰረት የጣለ የመሰዋትነት ትግል ያደረጉባቸው ቀናት ስለሆኑ በየአመቱ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በይፋ የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ ሆነው እንደሚውሉም አስረድተዋል።

"የወጣቶቹ መስዋትነት ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላ ኢትዮጵያ የነጻነት አየር እንዲመጣ የትግል ምዕራፍ የከፈተ ነው" ያሉት ደግሞ የባህርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ ናቸው።

የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ለአማራ ህዝብ ሲሉ መስዋትነት የከፈሉ ወንድሞቹን ራዕይ ለማሳካት ተግተው በመስራት ለፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲ መረጋገጥ ትግላቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ነጻ የትምህርት እድል እንዲመቻችና ቤት ለሌላቸው ደግሞ ተደራጅተው ቅድሚያ የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው መወሰኑንም ገልፀዋል።

ለሰማዕታት ወጣቶች አባይ ማዶ ከሰማዕታት ሀውልት እስከ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ያለው የአንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ መታሰቢያ እንዲሆንም ተሰይሟል።

በተጨማሪም በተለምዶ ገጠር መንገድ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ነሐሴ አንድ ተብሎ የተሰየመ የመታሰቢያ አደባባይ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም