መርማሪ ፖሊስ በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገ

68

አዲስ አበባ  ነሐሴ 01/2012(ኢዜአ) መርማሪ ፖሊስ በወንጀል ድርጊት በተጠረጠሩት አቶ እስክንድር ነጋ ላይ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገ።

ዐቃቤ ህግ ቀዳሚ የምርመራ መዝገብ በማስከፈቱ ተጠርጣሪው ባሉበት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል። 

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት አቶ እስክንድር ነጋ ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ባለፉት ዘጠኝ ቀናት አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት ዛሬ በዝርዝር ለችሎቱ አቅርቧል።

በዚህም የተለያዩ ማስረጃዎች ማሰባሰቡን አስረድቶ፤ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እና ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያሳይ ማስረጃ ማሰባሰቡን ገልጿል።

ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ውጤት፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት ሌሎች ተጠርጣሪ ግብረ አበሮችን መያዙን እንዲሁም የ37 ምስክሮች ቃል መስማቱንና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን እንዳሰባሰበም ገልጿል።

ነገር ግን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ትንተና፣ በወንጀሉ የሚጠረጠሩ ሌሎች ግብረ አበሮችን የመለየት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተነሳው ሁከት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስከሬን የምርመራ ውጤት፣ ለሁከትና ብጥብጥ ተጠርጣሪው ያደራጃቸውን ተጠርጣሪዎች መያዝና መመርመር፣ በግልና በመንግስት ተቋማትና ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ማወቅ የሚቀረው መሆኑን አስረድቷል።

ይህንን ለማከናወንም ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኛቸውን በተመለከተ ማስረጃ መገኘቱን በመገናኛ ብዙሃን ሲነገር እንደነበር በማስታውስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መሰጠት እንደሌለበት አስረድተዋል።

"ተጠርጣሪውን ወንጀል ሰርተሃል" ብሎ ለማመን የሚያስችል ማስረጃ እንዳልቀረበም ገልጸዋል።

ዋስትና እንዲከለከል የቀረቡት ምክንያቶች አሳማኝ እንዳልሆኑ በመግለጽ የደንበኛቸው የዋስ መብት እንዲጠበቅ ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ከጥርጣሬ በላይ የሆነ ማስረጃ ማሰባሰቡን በመግለጽ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብም የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ተከራክሯል።

ለሁከት የተደራጁት ተጠርጣሪዎች ከክፍለ ከተማ እስከ ቀጣና ድረስ በመሆናቸው፣ የደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ በመሆኑ፣ ህይወት በመጥፋቱና ንብረት በመውደሙ እንዲሁም ከስልካቸው የተገኘው ማስረጃ አዲስ ነገር ያሳየው በመሆኑ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ጥያቄ አቅርቧል።

ግራ ቀኙኝ ያዳመጠው ችሎቱ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሶ፤ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ አድርጎታል።

በዐቃቤ ህግ የቀረበውን የቀዳሚ ምርመራ መዝገብን በተመለከተ ሂደቱን ለማስቀጠል ለነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ዐቃቤ ህግ የማመልከቻና የምስክሮችን ዝርዝር ይዞ እንዲቀርብ በማዘዝ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም