ለኮሮናቫይረስ መከላከያ ንቅናቄው እውን መሆን ባለድርሻ አካላት አቅማቸውን አሟጠው መጠቀም አለባቸው

65

አዲስ አበባ  ነሐሴ 01/2012 (ኢዜአ) አገር አቀፉ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ንቅናቄ እውን እንዲሆን ባለድርሻ አካላት አቅማቸውን አሟጠው መጠቀም እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለድርሻ አካላቱ ጋር ከተወያዩ በኋላ አገር አቀፉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ በይፋ መጀመር ተበስሯል።

ለአንድ ወር የሚቆየው አገር አቀፍ የንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ ለአገራዊ ውሳኔዎችና ዜጎችን ከሚመጣው የሞት አደጋ ለመታደግ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።

ለንቅናቄና ለዘመቻው ስኬት የፖለቲካ አመራሮች፣ የኅብረተሰብ አደረጃጀቶች፣ የሃይማኖች አባቶችና ሌሎችም የበኩላቸውን እንዲወጡም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ኮቪድ ባስከተለው ችግር በመላ አገሪቷ ከ29 ሚሊዮን የሚልቁ ተማሪዎች ቤት ለመቀመጥ መገደዳቸውንም አንስተዋል።

በመጪው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማሩ ሂደት ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል መምህራንና ተማሪዎች ኮቪድ-19ን ለመከላከል ልዩ ትኩረት መስጠት እንደለባቸው ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት።

የማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄው ወረርሽኙ የሚያደርሰውን የከፋ ጉዳት መቀነስና አገራዊ አጀንዳዎችን ማስቀጠል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

በመከላከልና በግንዛቤ መፍጠር ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመዘናጋት ሳቢያ እየተፈጠረ ያለውን ጉዳት ለመግታት ከዚህ በላይ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

መንግስት ለስራው መቃናት የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍና ከለጋሾች የተገኙ የምርመራ መሳሪያዎች ለክልሎች እንዲከፋፈሉ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ነገር ግን በአንድ ወር በሚካሄደው የንቅናቄ ዘመቻ ትምህርትም ይሁን ሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ወደነበሩበት ይመለሳሉ ማለት አይደለም ነው ያሉት።

በንቅናቄው በሚገኘው ውጤት ገደቦችና እንቅስቃሴዎች ይወሰናሉ፤ እርምጃዎችም ይቀጥላሉ ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም ወረርሽኙን ለመከላከል መንግስት ጥረት ማድረጉንና ግንዛቤም መፈጠሩን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አገራዊ ንቅናቄውን ለማስተግበር መንግስት ምን እንቅስቃሴ አድርጓል ሲሉም ጠይቀዋል።

ስራው በመንግስት ብቻ የሚካሄድ ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ አክለዋል።

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለንቅናቄው ተግባራዊነት ሁሉም ያለውን አቅምና የሰው ኃይል አሟጦ መጠቀም ይገባዋል ብለዋል።

በአገሪቷ የሚገኙና በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ያልገቡ መሣሪያዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በተያዘው የነሐሴ ወር የሚደረገው የምርመራና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አገራዊ ውሳኔዎችን ለመወሰን የሚያግዝ በመሆኑም በትኩረት ሊተገበር ይገባል ነው ያሉት።

በምርመራ ዘመቻው 200 ሺህ ሰዎችን ለመመርመር፤ በቤት ለቤት ልየታም 17 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል።