ያለፉት ሁለት ዓመታት የለውጥ እርምጃዎች ለተያዘው የብልጽግና ጉዞ መሰረት የጣሉ ናቸው-- አቶ ርስቱ ይርዳው

67

ሀዋሳ ነሀሴ 1/2012 (ኢዜአ) ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግስት የወሰዳቸው ዘርፈ ብዙ የለውጥ እርምጃዎች ለተያዘው የብልጽግና ጉዞ መሰረት የጣሉ መሆናቸውን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ፡፡ 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በተጀመረው የክልሉ አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት የለውጥ እርምጃዎቹ የብልጽግና ጉዞ መሰረት ከመጣሉም በላይ ለዘመናት ህዝብን ሲያስመርሩ የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች  መመለስ የተጀመሩበት ነው።

ሃገራዊና የህዝብ አንድነትን ለማስጠበቅና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ሊያረጋገጥ የታሰበው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግድቡ የዚህ ትውልድ ኣሻራ በመሆኑ ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል ብለዋል፡፡

ግድቡ ከተጀመረበት አንስቶ አሁን ላለበት ደረጃ ለማድረስ የክልሉ ህዝቦች አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበረ አስታውሰው እስኪጠናቀቅ ድረስም የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ልማት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ለታሰቡ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለውን ድርሻ እንዳለው  ጠቅሰው መትከል ብቻ ሳይሆን እንዲጸድቁ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለውጡ ከጅማሮው በተለያዩ ፈተናዎች የመጣ  ቢሆንም በህዝቦች የጋራ መተባበርና ፍላጎት በርካታ ድሎች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በክልሉ ላለፉት ዓመታት ታፍነው የቆዩ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለመመለስ መንግስት ያደረገው ጥረት  የሲዳማ ህዝብ  ጥያቄ በህገ መንግስቱ መሠረት መፈጸሙ በማሳየነት ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ህዝብን የሚያዳምጥና እውነተኛ የፌዴራላዊ ስርዓት የሚከተል መንግስት ስለመኖሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

በሌሎችም አካባቢዎች እየተነሱ ያሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎች የህዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ አኳኋን ለመመለስ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑንና የምክር ቤቱ አባላት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል፡፡

የበጀት ዓመቱ ከስኬቱ ባሻገር ለዘመናት በቆዩ ጥያቄዎች ሰበብ ለውጡን በማይፈልጉ ቡድኖች ጠንሳሽነት በገጠሙ  የጸጥታ ችግሮች የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን አውስተዋል፡፡

ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከፍ ለማድረግ እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች  የኮሮና ወረርሽኝ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ለመከላከል ትኩረት እንዲደረግም አቶ ርስቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ጉባኤው በዛሬው ውሎው በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሰራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት ማድረግ ጀምሯል።

የምክር ቤቱ ጉባኤ  በሶስት ቀናት ቆይታው የ2013 የስራ ዘመን በጀት፣ አዋጆችንና የካቢኔ ሹመት እንደሚያጸድቅ፣  የ2012 በጀት ዓመት አፈጻጻምና የተያዘው የስራ ዘመን ዕቅድ ላይ እንደሚወያይ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም