ስኳር ኮርፖሬሽን ከ15 ሚሊዮን ሊትር በላይ ኤታኖል ለፋብሪካዎች አሰራጨ

74

አዳማ ነሐሴ 01/2012(ኢዜአ) ስኳር ኮርፖሬሽን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ15 ሚሊዮን ሊትር በላይ ኤታኖል ለአልኮልና ሳኒታይዘር አምራች ፋብሪካዎች ማሰራጫቱን ገለጸ። 

የኮርፖሬሽኑ የምርታማነት ዓመታዊ ኮንፈረንስ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ በአዳማ ከተማ በተጀመረበት ወቅት እንተገለጸው ኮርፖሬሽኑ የአልኮል ምርት በሀገር ውስጥ በማምረት ከ21 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ችሏል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት  የተገኘው የስኳርና ኤታኖል ምርት ከፍተኛ  መሆኑን የስኳር ኮርፖሬሽኑ  ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዋዮ ሮባ በተለይም ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም በ2012 የበጀት ዓመት ከ15 ሚሊዮን ሊትር በላይ ኤታኖል በማምረት ለአልኮልና ሳኒታይዘር አምራች ፋብሪካዎች ማሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

ተዳክመው የነበሩ ነባር ፋብሪካዎችን ጭምር በመታደግና አዳዲሶቹን ወደ ስራ በማስገባት አምና ከነበረው ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የስኳር ምርት ጭማሪ ማምረት መቻሉንም  ገልጸዋል።

"አሁንም በርካታ ስራዎች ይቀሩናል" ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ሁሉንም አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች እስከ ቀጣዩ ዓመት ታህሳስ ወር ድረስ በሙሉ በማጠናቀቅ  ወደ ምርት የሚያስገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኦሞ ኩራዝ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ መግባቱን ያመለከቱት  አቶ ዋዮ፤ኦሞ  ቁጥር ሁለትና ሶስት፣ ከሰምና አርጆ ዲዴሳ ፋብሪካዎችም  ያለባቸውን ችግር  በመፍታት ወደ ምርት እየገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጣና በለስን ጨምሮ ኦሞ አንድና ኦሞ አምስት  ፕሮጄክቶችን ከተቋራጮች በመንጠቅ ለውጪ ኩባንያ በመሰጠቱ ግንባታቸው እየተፋጠነ  መሆኑን  በስምንት ወር ውስጥ በማጠናቀቅ  ስራ ለማስጀመር በመረባረብ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የኮንፈረንሱ ዓላማ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በኮርፖሬሽኑ የታዩ ስኬቶችን በቀጣዩ ዓመት ለማስቀጠል ያለመ ነው ያሉት ደግሞ በስኳር ፋብሪካ ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ተክሌ ናቸው።

በተለይም በሰው ኃይል ውጤታማነት ላይ የታዩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች መለየት ፈጣን መፍትሄ ለማስቀመጥ ጭምር እንደሆነ  አመልክተዋል።

የኮሮና ቫይረስ  ወደ ሀገር በመግባቱ ለማምረት ስጋት የነበረ ቢሆንም ፋብሪካዎቹ ስጋቱን በመቋቋም ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የስኳርና ኤታኖል ማምረታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ሀገሪቱ በኮሮና ምክንያት  ከውጭ ማስገባት የነበረባትን የአልኮል ምርት በሀገር ውስጥ በማምረት ከ21 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛር ማዳን መቻሉንም አስታውቀዋል።

ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስኳር  በማምረት የእቅዱን 73 በመቶ ማሳካት መቻሉንም አሰረድተዋል።

የስኳር ኮርፖሬሽን የቦርድ አባል ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው "ሀገሪቱ ለስኳር ልማት ተስማሚ የሆነ የአየር ፀባይ፣ለም መሬትና አቅም ያላት በመሆኑ በእውቀት ላይ ከሰራን በዘርፉ ልማት ከአፍሪካ ቀዳሚ እንሆናለን " ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ሊፈጽመው የሚችል እቅድ፣ በእውቀት፣ ቴክኖሎጅና ቴክኒካል ዘርፍ የበቃ የሰው ኃይል እንዲኖረው  በመደረጉ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም