ግድቡን ለፍጻሜ ለማብቃት እንደሚሰሩ በሀዋሳ ነዋሪዎች ገለጹ

54

ሀዋሳ፣ ሐምሌ 1/2012 (ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁን የደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያዊያን እንደወትሮ በመተባበር ግንባታው ለፍጻሜ ማብቃት እንደሚቻሉ ማሳያ መሆኑን የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ  የሚውል እስከ 100 ሺህ ብር ተጨማሪ ቦንድ ግዥ  መፈጸማቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በሃዋሳ ከተማ በተዘጋጀ የቦንድ ግዥ መርሀ-ግብር  የ10 ሺህ ብር ቦንድ ሲገዛ የነበረው ወጣት ስንታየሁ ጴጥሮስ  በሰጠው አስተያየት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከቁርሱ  በመቀነስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሷል።

ከትምህርት በኋላ በህትመት ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ የገለጸው ወጣት ስንታየሁ ቀደም ሲልም የአምስት ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት አስተዋፅኦ ማድረጉንም ጠቅሷል።

የህዳሴው ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰው ሂደቱን ለማደናቀፍ የሀገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደሩ ባሉበት ወቅት ነው፤ ይህም ተባብረን ከሰራን ከፍጻሜ ማብቃት ማሸነፍ  እንደምንችል ማሳያ ነው ብሏል።

ግድቡ ለፍፃሜ በቅቶ የሚፈለገውን ኃይል ማመንጨት እስኪችል ድረስ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በዕለቱ ቦንድ እንደገዙ የተናገሩት  አቶ ደምሴ ቤንዝሌ ከዚህ በፊት በሁለት ዙር የ15 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን አውስተዋል።

ከዚህ በፊት ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩት በተስፋ ብቻ እንደነበር ገልፀው "አሁን ላይ በተጨባጭ ለማየት በመቻላችን የበለጠ ድጋፍ ለማድረግ መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሳን ይህን ግድብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ታላላቅ ሥራዎችን መስራት እንችላለን፤ ግድቡ ተሸጧል በማለት ያልሆነ አሉባልታ የሚነዙ ኃይሎችን ወደ ጎን በመተው ግድቡን ለማጠናቀቅ በአንድነት መነሳት አለብን" ብለዋል ፡፡

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ሁሉም ዜጋ  በመተባባር የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንደተቻለ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ የበራ መኮንን ናቸው።

ከዚህ በፊት የ70 ሺህ ብር ቦንድ ገዝተው እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ግድቡ ለዚህ በመብቃቱ ተደስተው ተጨማሪ የ100 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ድጋፋቸው እስከ ግድቡ ግንባታ ፍፃሜ የሚቀጥሉ ያመለከቱት አቶ የበራ "በልጆቼ ስምም ቦንድ እገዛለሁ" ብለዋል።

ወይዘሮ ታደለች አጋሞ  በበኩላቸው ከአከባቢያቸው ነዋሪ እናቶች ጋር በመተባበር በልማት ቡድናቸው አማካኝነት ከዚህ በፊት የአምስት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

አሁን ደግሞ የ15 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ጠቅሰው  "የአባይ ግድብ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም የሚተርፍ በመሆኑ እስከ መጨረሻው ድጋፍችንን አናቋረጥም " ብለዋል።

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ ወይዘሮ መአዛ ባጢሶ በከተማውና አካባቢዋ የሚኖሩ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እስካሁን ለግድቡ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም