በተያዘው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዷል

85

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 30/2012 ( ኢዜአ) በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ መታቀዱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

ለእቅዱ ስኬትም በተለይ የመድሐኒት ዘርፉ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል ተብሏል።

የመሰረተ ልማት መጠናከር፣ በቀላሉ ሰልጥኖ ወደ ስራ መግባት የሚችል የሰው ሃይል፣ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በምቹ አጋጣሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

በሌላ በኩል የገበያ ተደራሽነት እያደገ መምጣትም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

እነዚህንና ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዷል።

በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለስኬት የሚያበቁ ምቹ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት እቅዱ መያዙን  የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አንተነህ አለሙ ይናገራሉ።

የቂሊንጦ የመድሐኒት (ፋርማሲዩቲካል) ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፈው ዓመት ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ነው።

በመሆኑም በፓርኩ የመድሐኒት አምራችነት መሳተፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህም አይነተኛ የኢንቨስትመንት መሳቢያ አማራጭ ሆኖ ለተያዘው እቅድ ስኬት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን አቶ አንተነህ ገልጸዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በዓለም የምግብ ነክ ምርቶች ፍላጎት መጨመሩንና ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስፋት ወደ ምግብ ምርት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

አዲስ የኢንቨስትመንት አማራጭ ከመፈለግ ባለፈ የአገር ውስጥ ባለህብቶች ኢንቨስትመንትን የሚያሳድጉ ስራዎች እንደሚሰሩና ለዚህም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎችን የማስተዋወቅ ስራም በስፋት ይከናወናል ብለዋል።

በኢንቨስትመንት ተቋማት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስፈልገው የጤና ጥንቃቄ እርምጃዎችና ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም