በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ዲጂታል የጤና ፈጠራና መማሪያ ማዕከል ተከፈተ

89

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 30/2012 ( ኢዜአ) በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የአገሪቱን የጤና አገልግሎትና የመረጃ አያያዝ ሥርዓት የሚያዘምን የዲጂታል ጤና ፈጠራ መማሪያ ማዕከል ተከፈተ።

ማዕከሉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ዛሬ በጋራ ከፍተውታል።

ማዕከሉ ከቢልና ሜሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን በተገኘ የ25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ  መገንባቱ ተገልጿል።

ዶክተር ሊያ  በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ በጤናው ሴክተር ለምተው የሚተገበሩ ሶፍት ዌሮችን በተጠቃሚው ፍላጎት  ላይ ለመመስረት ያስችላል።

የለሙትንም ሶፍትዌሮች በዛላቂነት ለመተግበርና ለመደገፍ እንዲሁም በቂ አቅም በመፍጠር የመንግሥትን ባለቤትነት በማረጋገጥ  ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በሙያው የሰለጠኑ ወጣቶችን በማበራከት በሥራ እድል ፈጠራ ላይም አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

የማዕከሉ የድጋፍ መረጃ ማዕከልም በትግበራ ላይ ባሉ ሲስተሞች ተጠቃሚዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚያገኙበት አስታውቀዋል።

በዚህም ከሌሎች አገሮች ልምድ በመቀመርም በዘርፉ እስከ 85 በመቶ ያሉትን ቀላል ችግሮች በማዕከሉ ለመፍታት ዕቅድ መያዙን ነው ያስረዱት።

ጎን ለጎንም ማዕከሉ ሥልጠናዎች በሚሰጥበት ሁኔታ መደራጀቱን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

ከዚህም በኋላ በጤናው ሴክተር የሚተገበሩት ሶፍትዌሮች በማዕከሉ ተፈትሸውና ከሌሎች የጤና አገልግሎት ሥርዓት ጋር መጣጣማቸው ይመሳከራል ብለዋል።

በቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን የአፍሪካ የጤና ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ዘውዱ ማዕከሉ የአገሪቱ የጤና መረጃ ሥርዓት በማዘመንና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ለማጎልበት አስተዋጽፆ እንዳለው ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች ድጋፍ የሚሰጠው ማዕከል የደቡብ ለደቡብ ትሰስር ማሳያ ሆኖ እንደሚያገለግል  አስታውቀዋል።

በቀጣይም ፋውንዴሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ዶክተር ሰለሞን ለማዕከሉና በሌሎች የጤናው ዘርፍ ሥራዎች ላበረከቱት አስተዋጽዖ በመድረኩ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፤ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም