በምስራቅ ወለጋ ዞን 13 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኞችን ጨምሮ 176 ሚሊዮን ችግኝ ተተከለ

52

ነቀምቴ፣ ሐምሌ 30/2012 (ኢዜአ) በምሥራቅ ወለጋ ዞን 13 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኞችን ጨምሮ ከ176 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የተፋሰስና የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ደሣለ በለታ እንደገለፁት በዞኑ በተያዘው ክረምት 176 ነጥብ 1 ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞች ተተክለዋል ።

ከተተከሉት ችግኞች መካከል 20 ሚሊዮኑ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ቀን የተተከሉ መሆናቸውን ቡደን መሪው ተናግረዋል ።

ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ለምግብነት የሚያገለግሉ 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኞችም በተከላው ተካተዋል ።

ችግኞቹ ፀድቀው ለታለመላቸው አገልግሎት እንዲውሉ በሁሉም ቀበሌዎች በልማት ቡድንና በጎረቤት ሕዝቡን በማስተሳሰር አጥር በማጠር፣ በመንከባከብና በመጠበቅ አሳድገው ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ አካባቢ የሚያወርሱበት አሰራር ተዘርግቷል ።

የጎቡ ሰዮ ወረዳ የኦንጎቦ በካኒሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገዲሣ ሉጬ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው አንድ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ በመትከል አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራን ከግብ ለማድረስና የአየር ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመከላከል የተከሉትን ችግኞች በአግባቡ አርመውና ኮትኩተው በማሳደግ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ገዛኸኝ መንግሥቱ ናቸው፡፡

ሌላው አርሶ አደር ፈየራ በቀለ በበኩላቸው የተተከለውን ችግኝ ዙርያውን በማጠር ፣ በመኮትኮትና የቅርብ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል ።

በዞኑ በ2011 ዓ.ም ከተተከሉት ችግኞች መካከል 89 በመቶ መጽደቃቸውን ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም