በአማራ ክልል 3. 7 ሚሊዮን ቤቶችን ተደራሽ የሚያደርግ የኮሮና መከላከል ዘመቻ ነገ ይጀመራል

154

ባህርዳር ፣ ሃምሌ 30/2012  ( ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚካሄደው ክልላዊ የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ዘመቻ በሁሉም ወረዳዎች ሶስት ነጥብ ሰባት ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዋለ በላይ እንደገለፁት  ዘመቻው በትክክለኛ መረጃ ተመስርቶ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስችል ነው።

የንቅናቄው ዋና ዓላማ ማህበረሰብ ተኮር የግንዛቤ ፈጠራ ማካሄድ፣ የተጠናከረ ምርመራ ማድረግ፣ የተቋማትን ዝግጁነት ማረጋገጥ፣ መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ማሻሻልና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጎልበት የሚረዳ ነው ።

ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት በሚካሄደው የማህበረሰብ ንቅናቄ ዘመቻ ኮሮናን በመከላከል ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አሰራር መሆኑን አስረድተዋል ።

የንቅናቄ ዘመቻው በክልሉ የሚገኙ 3 ነጥብ 7 ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ በበርካታ ህዝብ ግንዛቤ በመፍጠርና ሌሎች የመከላከል ተግባራት በማከናወን የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ተናግረዋል ።

በተጨማሪም ከ42 ሺህ በላይ የኮሮና ቫይረስ ምልክት የሚታይባቸውን ሰዎች እንዲመረመሩ በማድረግ የበሽታው ስርጭት ያለበትን ሁኔታ በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለመለየት የሚያስችል ስራ ይከናወናል።

የንቅናቄ ዘመቻውን ለማሳካትም ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያሉት የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብም የዘመቻውን አስፈላጊነት በመገንዘብ በየአካባቢው ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ናሙና በመስጠትና ትምህርቱን በመቀበል ለስኬታማነቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

የሚዲያና የኮምዩኒኬሽን ባለሙያዎችም የንቅናቄ ዘመቻው ዓላማ በማሳወቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላብራቶሪ ዳይሬክተር አቶ ማንአምኖት አገኘ በበኩላቸው የናሙና ምርመራ ስራውን ለማሳካት ስምንት የምርመራ ማዕከላት ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

አሁን ከተያዘው ሰፊ እቅድ ጋር ተያይዞ የደብረ ማርቆስና የመተማ ሆስፒታሎች አስፈላጊው የምርመራ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ሲሆን የባለሙያና ሌሎች ዝግጅቶች መጠናቀቁንም ተናግረዋል።

በአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት የሬዲዮ ጋዜጠኛ በለጠ ጥላሁን በበኩሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በማከናወን የአስተሳሰብ ስርጸት ማምጣት ያስፈልጋል ብሏል ።

በነገው እለት የሚጀመረውን የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ዘመቻ እንዲሳካም ስለ ዘመቻው ፋይዳና ጠቀሜታ በዜናና በፕሮግራሞች አዘጋጅቶ በማስተማር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግሯል።

 የመንግስት ኮምዩኒኬሽን የህትመት አዘጋጅ ባለሙያ አቶ ወለጋ በላይ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በዓለምም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ ስጋት መፍጠሩን እያየን ነው በማለት ተናግሯል።

ይህን ችግር መቋቋም የሚቻለው ሁሉም ህዝብ ራሱን፣ ቤተሰቡንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ከኮሮና ለመጠበቅ በቁርጠኝነት ሲንቀሳቀስ ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለዚህም ከክልል እስከ ወረዳ ያለውን የኮሚዩኒኬሽን አመራርና ባለሙያ በመጠቀም ተከታታይ ትምህርት በእምነት ተቋማት፣ በስራ ቦታና ሌሎች ህብረተሰቡ በሚሰባሰብባቸው አካባቢዎች ለመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም