ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አካባቢን በመፍጠር የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ

79

ሆሳዕና ሐምሌ 30/2012 (ኢዜአ) ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመሰረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመሰረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትርና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ስራ ጎን ለጎን ሀገራዊና ማህበረሰባዊ አገልግሎትን በስፋት ማከናወን አለባቸው።

የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሀ ሙሌት መጠናቀቅ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት ወደ ነበረው የአንድነት መንፈስ የመለሰና መላውን ህዝብ ያስደሰተ እንደነበር ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድቡ እስከሚጠናቀቅም ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት የነበረውን ተሳትፎ በማጠናከር ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው በሀገር ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ ስነስርዓትን መሰረት በማድረግ ዩኒቨርሲቲው 500 ሺህ የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በማዘጋጀት እየተከለ አንደሚገኝ ጠቁመዋል።

እስከ አሁን መላውን የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በማሳተፍ ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል 300 ሺህ መተከሉን ተናግረዋል።

የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁም ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ጠቁመው አምና ከተተከሉ ችግኞች 85 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ጠቁመዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ዲንና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር የቦርድ አባል ዶክተር ጸደቀ ላምቦሬ እንደገለጹት የተተከሉት ችግኞችን ተንከባክቦ ለማጽደቅ ለእያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተቆጥሮ እንደሚሰጥ ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም