የኢትዮጵያ አየር መንገድ 302 የአቪዬሽን ሙያተኞችን የፊታችን ቅዳሜ ያስመርቃል

38
አዲስ አበባ ሓምሌ 4/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቬዬሽን አካዳሚ 302 የአቪዬሽን ሙያተኞችን የፊታችን ቅዳሜ ያስመርቃል። አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው አካዳሚው የፊታችን ቅዳሜ  በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 302 የአቪዬሽን ሰልጣኞችን ያስመርቃል። ተመራቂዎቹ በንግድ ሥራ፣ በአውሮፕላን ጥገናና በአውሮፕላን አብራሪነት የሰለጠኑ መሆናቸውን አየር መንገዱ ገልጿል። በምረቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአየር መንገዱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምን ጨምሮ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሏል። ከምርቃው መርኃ-ግብር በኋላም አየር መንገዱ ለሰራተኞቹ በአዲስ አበባ ቦሌ አራብሳ ሊያስገነባ ያቀደውን የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩን የሚያበስር ስነ-ስርዓትም ይከናወናል። አየር መንገዱ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነታቸውን እንደገና ማደሳቸውን ተከትሎ ከቀናት በኋላ ወደ አስመራ ቀጥታ በረራ እንደሚጀምር አስታውቋል። ከ70 ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በአሁኑ ወቅት በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በደንበኞች መስተንግዶ እና በሽያጭ ሙያ ስልጠናዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተቋም ሆኗል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም