በተለያዩ አገራት ሆነው አገር ለማጥፋት የሚቀንቀሳቀሱ አካላትን እንደሚያወግዙ የኦሮሚያ ወጣቶች ገለጹ

32

አዲስ አበባ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) በተለያዩ አገራት ሆነው ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ሕዝብን እርስ በርስ ለማጋጨት የሚቀሰቅሱ ኃይሎችን እንደሚያወግዙ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ወጣቶች ገለጹ።

የኦሮሞ ወጣት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ይገነባል እንጂ አያት ቅድመ አያቶቹ ያቆዩዋትን አገር አያፈርስም ብለዋል፡፡

ከወጣቶቹ መካከል ወጣት ስለሺ ደቻሳ፣ መሳይ ትኩ እና አዲሱ ዑርጋ ህወሓት ለ27 ዓመታት የአማራና ኦሮሞ ህዝቦችን ለማጋጨት በሃሰተኛ ትርክቶች ህዝቡን ለመከፋፈል ሲሰራ መቆየቱን ይገልጻሉ።

የኦሮሞ ወጣት ከሌሎች የአገሪቱ ወጣቶች ጋር ታግሎ ለውጥ ቢያመጣም የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በማደናቀፍ ወደኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ኃይሎች እንዳሉ ገልጸዋል።

በቅርቡ የተከሰተው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ሃጫሉን መግደል ብቻ ሳይሆን የኦሮሞና አማራን ህዝቦች በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለመ እንደነበርም ተናግረዋል።

የአርቲስቱን ሞት ተከትሎም የመንግስት አመራረርና የጸጥታ አካላትን ጨምሮ በርካቶችን ባሳተፈ መንገድ በተቀናጀ አግባብ የንጹሀን ግድያና ንብረት ማውደም ተግባር መፈጸሙን የገለጹት ወጣቶቹ፤ ድርጊቱ ከኦሮሞ ባህልና እሴት የወጣ በመሆኑ እንደሚያወግዙት አመልክተዋል።

የኦሮሞ ጥያቄ የፍትህ፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ እንጂ ከሌላው ብሔር መነጠል እንዳልሆነ ያመለከቱት ወጣቶቹ፣ ኢትዮጵያ ትፍረስ የሚሉ አካለትም በኢትዮጵያ ምስረታና የአገር ሉዓላዊነት ላይ ኦሮሞ የነበረውን ታሪክ የማያውቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለያዩ አገራት ሆነው አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ ትርምስ ለመፍጠርና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚቀሰቅሱ ኃይሎችንም እንደሚያወግዙ ነው ወጣቶች የተናገሩት።

በተፈጸሙት የጥፋት ተግባራት ቀድሞ ኦሮሞን ሲበድሉ የነበሩ አካላት እጃቸው አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

አንዳንዶች ለውጡ እንዲመጣ ስንታገል ነበር በሚል አንዱን ከሌላው በማጋጨት ሰው ሲያስገድሉና ንብረት እንዲወድም ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ተግባራቸው ቀድሞውንም ለስልጣን እንጂ ለህዝብ እንዳልታገሉ ማሳያ ነው ሲሉ ወጣቶቹ ተችተዋል።

መንግስትም እነዚህን ኃይሎች ተከታትሎ ከመያዝ ባለፈ በህግ ማስከበር ላይ በትኩረት እንዲሰራ ነው የጠየቁት።

በህግ ጥላ ስር የሚገኙ የወንጀል ተጠርጣሪዎችም በህዝብ አመጽ ከእስር ለመውጣት እንደሚፈልጉ ወጣቶቹ ጠቁመው፤ መንግስት በዚህ በኩል ድርድር ሊያድርግ እንደማይገባ አመልክተዋል።

በመንግስት መዋቅር ተሰግስገው ሕዝብን ለማጋጨት የሚሰሩ ኃይሎችንም መንግስት አጣርቶ ተጠያቂ ማድረግ አለበት ብለዋል።

 ግለሰቦችና የተለያዩ አካላት በሃገሪትዋና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጦርነት አዋጅ የኦሮሞ ህዝብና ቄሮን አይወክልም ወታት  ስለሺ ደቻሳ ነው፡፡

 የኦሮሞ ወጣቶች ኢትዮጵያ አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸው አፍስሰው ያቆዩልን ሃገር እንገነባለን እንጂ አናፈርስም የሚለው ደግሞ መሳይ ትኩ ነው፡፡

     የተሳሳተ ትርክቶች  በማውራት ህዝቡ አንድ ብሄር ላይ እንዲዘምት ለማድረግ ነው የሚለው ወጣት አዲሱ ዑርጋ ይህን ለመቅረ ፍ ትውልድ መስራት አለበት ብሏል

ከለውጥ በኋላ በተፈጸመ የጥፋት ተግባር የየትኛውም ብሔር ተወላጅ ላይ ጉዳት ቢደርስ ችግሩ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እስከተፈጸመ ድረስ ተጠያቂው የኦሮሞ ወጣት በመሆኑበቀጣይ ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጸም አንፈቅድም ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ወጣቶችም ከስሜታዊነት ተላቀው ከሌሎች ብሔር ተወላጆች ጋር ኢትዮጵያን በአንድነት እንዲገነቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ዜጎችም ድጋፍ ለማድረግ ኮሚቴ እያቋቋሙ መሆናቸውንም ወጣቶቹ ተናግረዋል።

መንግስት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ከማቋቋም ባለፈ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፉና ከጀርባ ያሉ አካላትን ችላ ማለት እንደሌለበትም  ስለሺ ደቻሳ ።

ማህበረሰቡና ወጣቱ የጥፋት ተሳታፊዎችን ለሕግ አሳልፎ በመስጠት ህግ በማስከበር ሥራው የበኩላቸውን እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

ጥፋቱን ያሰማራውን አካል መንግስት እንዲጠይቅ ያሳሰቡት ወጣት ደቻሳ ጠይቋል፡፡

ከለውጡ በኋላ የተጎዳውም ሆነ የተጠቀመው የኦሮሞ ህዝብ በመሆኑ ያሉብንን ችግሮች ከሌሎች ወንድሞቻችን ጋር በመሆን በውጭ ሆነው ጠብ የሚጭሩትን መታገል አለብኝ ያለው ደግሞ ወጣት መሳይ ትኩ ነው፡፡

 በተቻለን አቅም  የተጎዱ ወገኖችን ማቋቋምና ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ በጋራ እንሰራለን ያለውም ወጣት አዲሱ ዑርጋ ነው፡፡