በክልሉ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት ይሰራል... አቶ ተመስገን ጥሩነህ

87

ደብረ ማርቆስ፤ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። 

በምስራቅ ጎጃም ዞን   403 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚህ ወቅት  እንዳሉት እየጨመረ የመጣውን የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎችን አቅም በፈቀደ መንገድ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ  ነው።

በተለይም የመንገድ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ መስኖ ፣ የጤናና ሌሎችም  የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  እንቅስቃሴ የሚያፋጥኑ የልማት ተግባራት ተደራሽ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተመረቁት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችም የማህበረሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለመመለስ  የሚያግዙ  መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ የህብረተሰቡን የመልማት ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተገነቡ በመሆናቸው ችግር ከመፍታት  ባሻገር በቀጣይ ለሚነሱ የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት  ጥንካሬን የሚፈጥሩ ናቸው።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ያለውን እምቅ የልማት ሃብትና ለዚህም ስራ  ቀናኢ የሆነ ማህበረሰብ በማንቀሳቀስ በልማት ግንባር ቀደም ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀስ አካባቢ ነው ብለዋል።

አቶ ተመስገን እንዳመለከቱት  የክልሉ መንግስትም ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን የመብራት፣ ውሃ እና ሌሎች የልማት  ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረት ይደረጋል።

በክልሉ የኢንቨስትመንት መሬት የወሰዱ ባለሃብቶች ግንባታቸውን በፍጥነት አጠናቀው ወደ ስራ በመግባት ምርታቸውን ለተጠቃሚ ማቅረብና የስራ እድል እንዲፈጥሩ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም አብራርተዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው የዞኑን ህዝብ የመልማት ፍላጎትን ለማሳካት እንዲያግዝ  የ403 ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ  ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅም በመንግስትና  ህብረተሰቡ ድጋፍ የተገኘ  ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ገልጸዋል።

እነዚህ የልማት ጥያቄዎች የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያግዝ  ቢሆንም አሁንም  ያለውን የመብራት፣ የአውሮፕላን ማረፊያና  የይዳ ጨሞጋ መስኖ ግድብ ግንባታ ከዞኑ አቅም በላይ በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠቁመዋል።

የሞጣ ከተማ ነዋሪ አቶ ቢለው አበጀ በሰጡት አስተያየት  በከተማው የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም የረጅም ጊዜ ጥያቄ እንዲፈታ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የተገነበው የውሃ ተቋምም ንፅህናውን ካልጠበቀ የጉድጓድ ውሃ እንዳላቀቃቸው አመልክተው፤ በዚህም ቤተሰቦቻቸው ለውሃ ፍለጋ ከ2 ሰዓት በላይ ያደርጉት የነበረውን ድካም አስቀርቷል ብለዋል።

በከተማው የተገነባው ሆስፒታል የተሻለ ህክምና በአቅራቢያቸው ለማግኘት እንዳስቻላቸው የገለጹት ደግሞ  የደብረ ወርቅ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እመናት ጣሴ ናቸው።

የሆስፒታሉ መገንባትም ከዚህ ቀደም ለከፍተኛ ህክምና ፍለጋ ደጀንና ደብረ ማርቆስ  በመሄድ ያደርጉት የነበረውን የጊዜም ሆነ ወጪ የሚያስቀርርላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከተመረቁት መካከል የመንገድ፣ ድልድዮች፣ የገበያ ሼዶች፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም