በድሬዳዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ11 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል ተመቻችቷል

47

ድሬዳዋ ሐምሌ 29/2012(ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኮሮና ወረርሽኝ ከመከላከሉ በተጓዳኝ ከ11 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል መመቻቸቱን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ገለጹ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ሁለተኛ የስራ ዘመን 44ኛ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው።

ጉባኤው ዛሬ ሲጀመር ምክትል ከንቲባው ባቀረቡት ሪፖርት  ኮሮና ለመከላከል ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር፣ ፣ቤት ለቤት በመዘዋወር የመለየት ፣የምርመራ ተግባራት በማከናወን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አበረታች ሥራ ተስርቷል ብለዋል፡፡

በተለይ በቫይረሱ ሣቢያ በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሯቸው እንዳይናጋ የተለያዩ በጎ አድራጊዎች  ማዕድ በማጋራት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከፌደራል መንግስት የተደረገው ድጋፍ ጨምሮ 120 ሚሊዮን ብር የሚገመት  ዱቄትና የንጽህና መጠበቂያዎች ድጋፍ ለሚፈልጉት መሰጠቱንም አመልክተዋል፡፡

በተጓዳኝም በበጀት ዓመቱ ከ11 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ እድል በማመቻቸት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም  በ77 ኢንተርፕራይዞች  ለተደራጁ ወጣቶች 8 ሚሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን  በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

አስቀድመው ለተደራጁ 420 ኢንተርፕራይዞች የ140 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር በመፍጠር ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉም ተመልክቷል።

ብድር በማስመለስ በኩል 109 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትና የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በገጠርና በከተማ የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለማቃለል የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው ተብሏል፡፡

በምክር ቤቱ የማህበራዊ፣ የከተማ ልማት ፣ ኮንስትራክሽንና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሰላማዊት አስፋው የካፒታል ፕሮጀክቶች መጓተትና መታጠፍ ቅሬታ እየፈጠሩ በመሆኑ መስተካከል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች ግንባታ ጥረት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው ፤ የገጠር የሥራ እድል ፈጠራ፣ ለወጣቶች የተገነቡ ቀሪ  የመሸጫና የማምረቻ ሼዶች በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ህገ-ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ እየተባባሰ በመምጣቱ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ምክትል ከንቲባውና የካቢኔ አባላት በጉባኤው የተነሱት ከፍተቶች በቀጣይ ለማስተካከል የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጉባኤ ነገም ቀጥሎ በተያዘው የበጀት ዓመት  የሥራ እድልና ማስፈጸሚያ  በጀት እንዲሁም የተለያዩ ሹመቶች ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም