ለምንገነባት አገር ጠንካራ የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት ያስፈልጋል... ኢንጂነር ታከለ ኡማ

59

 አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ)"ጠንካራ የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት ከሌለ የምንፈልጋትን አገር መገንባት የማይታሰብ ነው" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

"ህዝብን ከልብ ማገልገል አገርን የመውደድ መገለጫ ነውም" ብለዋል።

በአዳማ ከተማ ከሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በክፍለ ከተማ ለሚገኙ ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች ሲካሄድ የነበረው ሥልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

ሥልጠናው በ2013 በጀት ዓመት የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግና ተገልጋዩን ህብረተሰብ በብቃትና በስነ-ምግባር ማገልገል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በሥልጠናው ማጠናቂያ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያም ሰጥተዋል።

ምክትል ከንቲባው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የከተማ አስተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው በአገልግሎት አሰጣጥ ውጤት ማምጣት ነው ብለዋል።

ለዚህም የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ጠንካራ ሥርዓትን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ይህም እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ ምቹ የሥራ ሁኔታ የመፍጠር፣ በሠራተኞች የሚነሳውን የመኖሪያ ቤትና ሌሎች ጥያቄዎች የመመለስ እንዲሁም አደረጃጀትን የመቀየር ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው አገልግሎት አሰጣጡን ከማሳደግ ባለፈ በአገር ደረጃ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ያለው አስተዋጽኦ ወሳኝ እንደሆነም አመልክተዋል።

ያለ ጠንካራ ፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት የምንፈልጋትን ጠንካራ አገርና መንግሥት ለመገንባት

እንደማይቻልም ገልጸዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው አገሩን የሚወድ ከሆነ ከልብ በመነጨ ስሜት ህዝቡን ማገልገል ይኖርበታልም ብለዋል ምክትል ከንቲባው።

ሠራተኛው በአገልጋይነት መንፈስ መሥራቱ እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያዊነት ባህል እርስ በእርስ ተከባብሮና ተጋግዞ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ በበኩላቸው የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የማስፈጸም አቅም ላይ ጠንክሮ መሥራት ይገባል ብለዋል።

የደንበኛ አያያዝ ክህሎትን ማሳደግ፣ ብልሹ አሠራሮችን መታገልና በጥቅም አገልግሎትን ማግኘት የሚፈልጉ ተገልጋዮችን ማረምም ያስፈልጋል ብለዋል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በሥልጠናው የነበሩ ሐሳቦች የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው አገልግሎት አሰጣጡን፣ ደንበኛን የማክበርና በትጋት የማገልገልን አቅጣጫዎች በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ህዝብን ማገልገል ከልብ የመነጨ ሆኖ የውስጥ ተነሳሽነትን የሚፈልግ እንደሆነ ተሞክሮ የተወሰደበት ነውም ብለዋል።

በሥልጠናው ላይ 1 ሺህ 200 የሚሆኑ አመራሮች መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ቀጣይነት ባለው መልኩ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ላሉ ሠራተኞች ይሰጣል ተብሏል።

በአገር ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎችን አስመልክቶም በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ መደረጉ በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም