በጉባው ግድያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

80

አሶሳ፣ ሐምሌ 29 /2012(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ ሰሞኑን በንጹሃን ላይ በተፈጸመው ግድያ ተጠርጥረው የተየዙ ግለሰቦችን ለፍርድ ለማቅረብ የተቀናጀ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ፖሊስ እና ጠቅላይ አቃቢ ህግ ገለጹ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሃመድ ሃምኒል ለኢዜአ እንደገለጹት  ሰሞኑን  በጉባ ወረዳ በተፈጸመው ግድያ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 125 ደርሷል፡፡

ከመካከላቸውም 95  በግድያው መሳተፋቸው ማስረጃ የተገኘባቸው ናቸው ብለዋል።

ሌሎች 30ዎቹ ደግሞ ትላንት  እንደተያዙና በማንኩሽ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት  ቃላቸውን እየሰጡ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ከተጠርጣዎቹ መካከል ሶስቱ የጉባ ወረዳ አመራሮች እንደሚገኙበት ጠቁመው የጸረ-ሠላም ኃይሎችን ተልዕኮ  ለማክሸፍ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አስረድተዋል።

የጥቃቱ ዋነኛ ተልዕኮ ጉባ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ አራት ቀበሌዎችን አጠቃላይ የጸጥታ ኃይሉን በመበተን መንግስታዊ መዋቅር በማፍረስ ጸረ-ሠላም ኃይሎቹ የራሳቸውን አስተዳደር መተካት እንደሆነ የእስካሁኑ  ምርመራ እንደሚያመላክት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የተያዙት ግለሰቦች ጥቃቱን ለመፈጸም ሲያደርጉት የነበረው የሚያመላክት ሰነድና  የቪዲዮ ማስረጃዎች መገኘታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የቪዲዮ ማስረጃ ህብረተሰቡን  እርስ በርስ በማጋጨት አካባቢውን የማተራመስ እቅድን የሚያብራራ በአረብኛ፣ ጉሙዝኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ መረጃ እንደያዘ ጠቁመዋል፡፡

በጥቃቱ በክልሉ የሚገኙ የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጉህዴን) እና የበርታ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ለሠላም እና ለዴሞክራሲ (በህነንሰዴድ) አባላት እንደሚገኙበት ገልጸው ታጣቂዎቹ ተልዕኮው ከህወሃት እንደተሰጣቸው የፖሊስ ምርመራ እንደሚያመላክት አብራርተዋል፡፡

ለጊዜው ከአካባቢው የሸሹትን የጉህዴን እና በህኔንሰዴድ አባላት ጨምሮ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ 

ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ  ለማቅረብ ምርመራው ከጠቅላይ አቃቢ ህግ ጋር  በመቀናጀት እየተሠራ  ነው ያሉት  በአሁኑ ወቅት አካባቢው መረጋጋቱን አስታውቀዋል፡፡

የጸጥታ ኃይሉ በአካባቢው የተበታተኑ ሌሎች ጸረ-ሠላም ኃይሎችን ለመያዝ የሚደረገውን ክትትል ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ዋና ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ሰይድ ባበክር በበኩላቸው  የተደራጀ የጠቅላይ አቃቢ ህጎች ምርመራ ቡድን ተቋቁሞ ወደ መተከል ዞን በመግባት ስራ  መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በጉባ ወረዳ ሰሞኑን በንጹሃን ላይ በተፈጸመው ግድያ ተጠርጥረው የተያዙት ግለሰቦች ላይ የሚካሄደው ምርመራ ከጸጥታ ኃይሎች እና ከህብረተሰቡ የተቀናጀ እንደሆነ አመልክተዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ሰብዓዊ መብታቸው እየተጠበቀ መሆኑን አቶ ሰይድ ተናግረዋል።

በጉባ ወረዳ ሐምሌ 20 / 2012 ዓ.ም. ምሽት በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም