ዩኒቨርሲቲው የኦሮሞ ኪነ ጥበብን ለማሳደግ ልዩ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በነፃ ሊያስተምር ነው

40

ጅማ ኢዜአ ሐምሌ 29/2012 , ጅማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ኪነ ጥበብን ለማሳደግ ልዩ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ ነፃ የትምህርት እድል ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡

መታሰቢያነቱም ለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ለአርቲስቱ የመታሰቢያ ስነ ስርዓት አካሔዷል ።

 ዩኒቨርሲቲው የመታሰቢያ ስነ-ስርዓቱን ያካሄደው “ሃጫሉ የሀገር ተስፋ፣ የአንድነት፣ የሰላምና የፍትህ ድምጽ ነው” በሚል መሪ ሐሳብ ነው።

አርቲስት ሃጫሉ ከጅማ ህዝብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለውና ለአካባቢው ህዝብ እድገት የበኩልን የተወጣ አርቲስት መሆኑን በስነ ስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡

አርቲስቱ ለአጋሮ ልማት ህዝቡን ለማነሳሳት ‘አጋሮ አጋሮ’ የሚል ዘፈን፤ እንደዚሁም የጅማ ህዝብ ተለይቶ የሚታወቅበት ‘ሰኚ ሞቲ’ የሚሉትን ሙዚቃዎች ያበረከተ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ጅማ ዩኒቨርሲቲ የመታሰቢያ ዝግጅቱን ሲያካሄድ ለወደፊቱ እልፍ አእላፍ ሃጫሉዎችን ለማፍራት የሚኖረው ጠቃሜታ ትልቅ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ነው ተብሏል ።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ልዩ ሁነቶች ማካሄጃ የነበረውን ሁለገብ ስታዲየም “የሃጫሉ የሲቪክ ማዕከል” በሚል እንዲሰየም መደረጉን ገልፀዋል ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ማዕከል በኩል የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎቹ በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች ላይ እንዲታተሙ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው በሃጫሉ ስም የኦሮሞ ኪነ ጥበብን ለማሳደግ ልዩ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን ተቀብሎ ነፃ የትምህርት እድል መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል ።

በመታሰቢያ ዝግጁቱ ላይ በሃጫሉ ሙዚቃ ስራዎች ላይ ያተኮሩ ሦስት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በቀረቡት ፅሁፎች  ላይም ሃጫሉ የኦሮሞ ህዝብ መብትና አንድነት እንዲከበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረገ ታላቅ አርቲስት መሆኑን ተመላክቷል፡፡

በመታሰቢያ ዝግጅቱ ላይ የወለጋ፣ የመቱ፣ ቦንጋ፣ ወልቂጤና ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የአርትስት ሃጫሉ ወንድም ሲሳይ ሁንዴሳ፣ የሃጫሉ ጓደኞች፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞችና የጅማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል ።