በሰሜን ጎንደር ዞን በ1ሺህ 700 ሔክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ጎንደር ዞን በ1ሺህ 700 ሔክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ እየለማ ነው

ጎንደር (ኢዜአ) ሐምሌ 29/2012 በሰሜን ጎንደር ዞን በዘንድሮ የመኸር አዝመራ ለብቅል ፋብሪካዎች ግብዓት የሚውል ምርት ለማቅረብ ከ1 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በቢራ ገብስ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ ፡፡
የመምሪያው ሃላፊ አቶ አራጋው ገብረማርያም ለኢዜአ እንደተናገሩት አርሶ አደሩ በቢራ ገብስ ልማት በስፋት እንዲሳተፍ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በአርሶ አደሮቹ ጥራቱን ጠብቆ የሚመረተው የቢራ ገብስ ለብቅል ፋብሪካዎች ግብዓት የሚውል መሆኑን ገልፀዋል።
የቢራ ገብስ ልማቱ እየተከናወነ ያለውም በጃናሞራ፣ ዳባት፣ ደባርቅና በየዳ ወረዳዎች በሚገኙ 56 ቀበሌዎች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቢራ ገብስ ከለማው መሬት ውስጥም አንድ ሺህ ሄክታር መሬት በክላስተር እየለማ መሆኑን አመልክተው በቢራ ገብስ ልማቱም ከ3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ምርታማነትን ለማሳደግ ከ900 ኩንታል በላይ ''ሆልከር'' የተባለ ምርጥ ዘርና ከ2 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮቹ እንደቀረበላቸው ገልጸዋል።
አርሶአደሩ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም በመጀመሩ በአሁኑ ወቅት የቢራ ገብስ ምርታማነትን በሄክታር 27 ኩንታል ማድረስ መቻሉንም አስታውቀዋል።
አርሶ አደሮቹ ከሚያለሙት መሬት ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ የቢራ ገብስ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ አንደሚጠበቅ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
መምሪያው አርሶ አደሮቹ ለሚያመርቱት ምርት የገበያ ትስስር በመፍጠር በኩል ከጎንደር ብቅል ፋብሪካ ጋር በተፈጠረው ግንኙነት ከገበያ ዋጋ 15 በመቶ ጭማሪ በማድረግ እንዲረከባቸው ይደረጋል።
የጎንደር ብቅል ፋብሪካ በመቋቋሙ የገበያ ችግር ገጥሞን አያውቅም ያሉት በዳባት ወረዳ የወቅን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ማርሸት መኳንንት ናቸው፡፡
በዘንድሮ የመኸር አዝመራ በግማሽ ሄክታር መሬት ካለማሁት የቢራ ገብስ 13 ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውንም አርሶ አደሩ ተናግረዋል ።
ባለፉት ሶስት አመታት አምርተው በሸጡት የቢራ ገብስ የሁለት የእርሻ በሬ ባለቤት መሆን እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ በደባርቅ ወረዳ የሚሊገብሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ደምስ ማናዬ ናቸው፡፡
''ዘንድሮም በአንድ ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ የቢራ ገብስ እያለማሁ ነው'' ያሉት አርሶ አደር ደምስ የሰብሉ አበቃቀል አስደሳች በመሆኑ 26 ኩንታል ምርት እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡
የጎንደር ብቅል ፋብሪካ በአመት እስከ 200 ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ በግብአትነት እንደሚጠቀም ከፋብሪካው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡