ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአሜሪካ መንግስት ላደረገው የሕክምና መገልገያዎች ድጋፍ ምስጋና አቀረቡ

41

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካ መንግስት ለተደረገው ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን 250 የመተንፈሻ ቬንትሌተሮች እና ሌሎች ወሳኝ የሕክምና መገልገያዎች ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

እነዚህ መገልገያዎች የደረሱን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ብዛት በጨመረበት አሳሳቢ ጊዜ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ተመጣጣኝ የመከላከል እርምጃዎች መውሰዳችን እንዳለ ሆኖ፣ መዘናጋት እና ቸልታንም አስወግደን እጆቻችንን በሚገባ በመታጠብ የአፍና የአፍንጫ ጭምብሎችን በአግባቡ መጠቀምና ርቀታችን መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስት 250 የሚሆኑ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

መሳሪያዎቹ በኮቪድ-19 ምክንያት የፅኑ ህክምና ዉስጥ ለሚገኙ ህሙማን የሚያገለግል ሲሆን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይነር ድጋፉን አስረክበዋል፡፡