የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሻሻል እየተሰራ ነው

85

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የውሃ ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

በ2013 በጀት ዓመት ለውሃ ፕሮጀክቶች ማከናወኛ 4 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙም ታውቋል።

በኢትዮጵያ ደካማ የሆነውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም አሁንም ችግሩ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑ ይነገራል።

እስካሁን ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ደካማ መሆኑን የውሃ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር በሻህ ሞገሴ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በመሆኑም በ2013 በጀት ዓመት በገጠርም ይሁን በከተማ በስፋት የሚስተዋለውን የውሃ ችግር ለማቃለል የሚያስችሉ ስራዎች ተጀምረዋል ነው ያሉት።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለኮሚሽኑ ተመድቦለት የነበረው በጀት 184 ሚሊዮን ብር መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር በሻህ፤

በ2013 በጀት ዓመት ግን 2 ቢሊዮን ብር ከመንግስት እንዲሁም 2 ቢሊዮን ብር ከአጋር ድርጅቶች ተመድቧል ብለዋል።

የተያዘው 4 ቢሊዮን ብር በጀት በውሃ ልማት ዘርፍ የተያዙ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር  እንደሚያግዝ በመግለጽ፤ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁም ደካማ የነበረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ይረዳል ነው ያሉት።

ከ20 ሺህ እስከ 100 ሺህ የህዝብ ቁጥር ያላቸው የዘጠኝ ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶችም እስከ ታህሳስ የሚጠናቀቁ መሆኑንም ገልጸዋል።


በገጠር በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ 25 ሊትር፤ ለአንድ ቀን፤ ለአንድ ሰው ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በከተሞችም በአጭር ርቀት ቢቻል በግቢ ውስጥ ውሃ እንዲያገኙ ይደረጋል ነው ያሉት።

በገጠር ያለውን የውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያግዙ የ41 ፕሮጀክቶች ግንባታ በእቅድ መያዙንም ተናግረዋለ።

በሳኒቴሽን በኩልም አዲስ አበባን ጨምሮ በ22 የተለያዩ ከተሞች ጥናቱ መጠናቀቁንም ይፋ አድርገዋል።

ዶክተር በሻህ እንደገለጹት የውሃ አቅርቦት ችግር ያለባቸውንና በኮሮናቫይረስ ሊጎዱ ይችላሉ በተባሉ ከተሞች በ13 ሚሊየን ብር የፓምፕ ግዥና የውሃ አቅርቦት ስራ ተከናውኗል።

በ23 ከተሞች እኛ ድንበር አካበቢ ያሉትን ከተሞች ከኮሮና ለመከላከልና እና በዘላቂነት የውሃ ችግራቸውን ለመፍታት ከክልሎቹ ጋር በመነጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የፓምፕ፣ ጄኔሬተር፣ የፓይፕ ማስፋፋት እና የጥገና ስራዎችም  እንደሚከናወኑ ተገልጿል።