ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ

68

ሀዋሳ ፣ሐምሌ 29/2012  (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛትና በሌሎችም የገቢ ማሰባሰቢያ መረሃ ግብር በመሳተፍ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።

በክልሉ የብላቴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ደመላሽ ግርማ  ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት በዕለት ተዕለት ኑሮቸው  ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት በህዳሴ ግድብ ሊፈታ እንደሚችል እምነት እንዳለው ተናግሯል።

ለዚህ እውን መሆን እስካሁን የ2 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት የአቅሙን አስተዋፅኦ ማድረጉን ያመለከተው  ወጣቱ እስከ ግድቡ ግንባታ ፍፃሜ ድረስ በቦንድ ግዥ እና በሌሎች የገቢ አሰባሰብ መረሃ ግብር ተሳትፎውን እንደሚቀጥል ገልጸዋል። 

የግድቡ መጠናቀቅ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር በተለያዩ አማራጮች ህብረተሰቡን ለማነቃነቅ የተጀመረው ስራ መጠናከር እንዳለበትም አስተያየቱ ሰጥቷል።  

ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ የመንግስት ሠራተኛ አቶ አክሊሉ ወታንጎ  በበኩላቸው ከደመወዛቸው በአራት ዙሮች  ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው  በቀጣይም  የድጋፍ ተሳትፏቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መሳካቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው የገለጹት የቦርቻ ወረዳ ነዋሪው አቶ ሄኖክ ቶሎሳ ደግሞ ከአሁን በፊት ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪ በቅርቡ የ4 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አውስተዋል።  

በአለታ ጩኮ ወረዳ  በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ቆስጣ ቆልቻሞ የአባይ ወንዝን ለመገደብ ለተጀመረው ስራ እንደሌላው ዜጋ ሁሉ እሳቸውም የተሳተፉበት የጋራ አርማ በመሆኑ  የግድቡ ግንባታ  መጠናቀቅ በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። 

በራሳቸውና ቤተሰባቸው   ስም እስካሁን የ6 ሺህ 500 ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰው ለግድቡ ቀሪ ስራም የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ክልሉ  ሲዳማ ዞን በነበረበት በወቅት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ መደረጉን ቀደም ሲል ዘግበናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም