በህገወጥ ደላሎች ምክንያት የምርታችን ተጠቃሚዎች መሆን አልቻልንም

100

አርባምንጭ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን በሙዝ ግብይት ላይ ህገ ወጥ ደላሎች በሚፈጥሩት ተፅእኖ የምርታቸውን ተጠቃሚዎች መሆን እንዳልቻሉ አርሶ አደሮች ገለፁ ።

በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጋንታ ካንቻሜ ቀበሌ አርሶ አደር ተስፋዬ ግራ በሰጡት አስተያየት ከሙዝ ግብይት ስርዓት ጋር የተያያዙ ችግሮች ባለመፈታታቸው አሁንም የምርታችን ተጠቃሚዎች አልሆንም ብለዋል ።

ህገ-ወጥ ደላሎች ከሙዝ ተረካቢ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ዋጋውን እንደፈለጉት ከፍና ዝቅ እያደረጉ በልፋታችን ልክ እንዳንጠቀም እንቅፋት ሆነውብናል የሚል ቅሬታ አሰምተዋል ።

ጥራትን ታሳቢ ያላደረገ አንድ ዓይነት ዋጋ በመቁረጥ ከእለት ወደ እለት የጥራት ደረጃውን እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑንም አርሶ አደሩ ተናግረዋል ።

መንግስት በግብይት ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየት ደረጃ በደረጃ እንዲፈታላቸውም አቶ ተስፋየ ጠይቀዋል ።

በምዕራብ አባያ ወረዳ የዋጅፎ ቀበሌ አርሶ አደር ከበደ ፋንታ በበኩላቸው መንግስት ህጋዊ የሙዝ ግብይት ማዕከላትን ማቋቋም ባለመቻሉ የገበያ ዋጋን እያዋዠቀው ይገኛል ብለዋል፡፡

በነጋዴዎች እጅ የሚገኘው ሚዛን በየጊዜው ፍተሻና ቁጥጥር የማይደረግበት በመሆኑ አምራቹ በምዘና ወቅተ እየተጭበረበረ መሆኑንም ጠቁመዋል።


የሚመለከተው አካል ነጋዴዎች ፍትሃዊ በሆነ ዋጋ ከአምራቹ እንዲረከቡና አርሶ አደሩም ለምርት ጥራት ትኩረት እንዲሰጥ የግብይት ህግ ማዕቀፍ በመዘርጋት ገበያውን ማስተካከል አለበት ብለዋል።

በህገ-ወጥ ደላሎች በኩል የሚፈጸሙ የግብይት ችግሮች አርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን እውቅና ያላቸው ማህበራትና ዩኒየኖችንም የችግሩ ሰለባ አድርጎአቸዋል ያሉት ደግሞ የጋሞ ጎፋ ገበሬዎች አትክልትና ፍራፍሬ ግብይት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ዳርጮ ናቸው፡፡

ለዚሁ ደግሞ በመንግስት በኩል ደላሎቹ ህጋዊ ሆነው እንዲሠሩ አለማድረግና የግብይት ማዕከላት ማቋቋም አለመቻሉ እንደሆነ በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የሙዝ ነጋዴ የሆኑት አቶ ትግሉ ደመቀ በበኩላቸው አርሶ አደሩ ያልደረሰውን ምርት እያቀረበ በመሆኑ በገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን ባለመቻላችን የሚደርስብን ኪሳራ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ይህ ችግር እንዳይኖር አርሶ አደሩ የደረሰ ሙዝ ለገበያ እንዲያቀርብ ትምርት ማግኘት እንዳለበት ጠቁመዋል ።

በጋሞ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የግብርና ምርት ግብይት ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተሾመ ዳንኤል ተጠይቀው ዞኑ በሙዝ ምርት እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ በበጀት ዓመቱ ከ300 ሺህ ቶን በላይ የሙዝ ምርት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ከሙዝ ግብይት ስርዓት ጋር በተያያዘ መንግስትን ጨምሮ በነጋዴው፣ በደላላውና በአርሶ አደሩ በራሱ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

የሙዝ ጥራትን ለማስጠበቅ ለጫኝና አውራጅ እንዲሁም ለነጋዴዎችና አምራች አርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሲሠራ መቆየቱንም አውስተዋል፡፡

የግብይት ችግሩን ለመቅረፍ የግብይት ማዕከላትን በአርባ ምንጭ እና ምዕራብ ዓባያ ወረዳዎች ለማቋቋም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የታቀደ ቢሆንም በኮሮና ምክንያት ባለመሠራቱ ወደ 2013 ዓም እንዲተላለፍ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ገበያውን ለመቆጣጠር መኪኖች ሙዝ ጭነው ሲወጡ የሚመዘኑበት የምድር ሚዛን በምዕራብ አባያ ወረዳ በአንድ ባለሀብት በ5 ሚሊዮን ብር እንዲተከል ቢደረግም በነጋዴዎች እጅ የሚገኙ ሚዛኖችን በመፈተሽ ረገድ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል ።

ክፍተቱን ለማስተካከል በ2013 የበጀት ዓመት በትኩረት ይሰራልም ብለዋል ።

በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያና ምዕራብ ዓባያ ወረዳዎችን ጨምሮ በገረሰ፣ ዳራ ማሎ፣ ካምባ እና ጋርዳ ማርታ ወረዳዎች ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በሙዝ የተሸፈነ መሆኑን አቶ ተሾመ ተናግረዋል ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም