የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰሩ አካላትን እንደሚታገሉ የአርሲ ዞን ወጣቶች ገለጹ

89

አዳማ ኢዜአ ሐምሌ 29/2012 የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲባል የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰሩ አካላትን እንደሚታገሉ የአርሲ ዞን ወጣቶች ገለጹ።

ወጣቶቹ የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ ዙሪያ ከፌዴራልና ከክልሉ አመራሮች ጋር በአሰላ ከተማ እየተወያዩ ነው።

በውይይት ላይ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በዞኑ በተከሰተው የጸጥታ ችግር የደረሰውን ጥፋት ወጣቶቹ አውግዘዋል።

"የጥፋት ኃይሎች አጀንዳ ማስፈጸሚያ አንሆንም" ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች በከተማውም ሆነ በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።

የመለስ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ እንደተናገሩት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

ከዚህ ባለፈም አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ተያይዞ ጥንቃቄ በጎደለው እንቅስቃሴ ምክንያትም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭነት ስጋት ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ወጣቶች በማንኛውም ሁኔታ ለሃገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት መናጋት ተግተው ለሚሰሩ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሊሆኑ እንደማይገባም አሳስበዋል።

የአሰላ ከተማ ከንቲባ አቶ ገብሬ ኡርጌሶ በበኩላቸው የችግሩን መከሰት ተከትሎ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የአሰላ ወጣቶች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

"የአሰላ ከተማ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብና ኃይማኖት ተከባብሮ በሰላም የሚኖርበት የመልካም እሴቶች ባለቤት ነው"ያሉት ከንቲባው ህዝቡ ከገዛ ወንድሙ ጋር እንዲባላ የሚሰራውን የጥፋት ኃይሎች ሴራ ተከታትሎ ማክሸፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ጀማል በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት የአርሲ ዞን ሁሉም ህብረተሰብ በተረጋጋ ሰላም ተከባብሮ በመኖር ዘመናትን ያሳለፈ የተከበረ ታሪክ ያለው ነው።

የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ የተስተዋለው ሁከትና ግርግር የነጻነት ተምሳሌት የሆነውን ወጣት ስም የሚያጎድፍ ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል።

እየተካሔደ ባለው የውይይት መድረክ ላይ ከክልሉና ከፌዴራል የመጡ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከዞኑ 26 ወረዳዎች ከአሰላ ከተማና ከሶስት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ወጣቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም