የድሬዳዋ የጎርፍ ስጋት ወደ ዘላቂ ልማት ለመለወጥ ጥናት እየተካሄደ ነው

60

ድሬዳዋ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) የድሬዳዋ የወንዝ ተፋሰሶችና ጎርፍን ወደ ዘላቂ ልማት ለመለወጥ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን አስታወቁ።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለሚያካሄደው ለዚሁ ጥናት ማስፈጸሚያ ስድስት ሚሊዮን ብር በአስተዳደሩ ተመድቧል።

ዩኒቨርሲቲው ከአስተዳደሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጥናቱ መካተት ስላለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት በመከረበት ወቅት የባለሥልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሀመድ እንደገለጹት፤ ጥናቱን ሁሉም የድሬዳዋ ሴክተሮች ተቀናጅተው የሚተገብሩት የደቻቱን ወንዝ ልክ እንደ አዲስ አበባው የወንዝ ዳርቻና እንጦጦ ልማት ዕውን ሚሆን ነው ፡፡

ጥናቱ የድሬዳዋ ሁለንተናዊ ገጽታ የሚለውጥ ፣ የላኛውን የጎርፍ ምንጭ የሆኑ ተፋሰሶች ላይ ሰፊ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች በማከናወን የአርሶ አደሩን የመስኖ ልማት ለማፋጠን እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ሲያደርስ የቆየው የደቻቱን ወንዝ ዳርቻ ለሀገርና ውጭ ቱሪስቶች በሚያመች መንገድ ማልማት ፣ ሰው ሰራሽ ሀይቅ መፍጠርና የድሬዳዋ ኢንቨስትመንት ፋሰት ወደ ሚፈለገው ከፍታ ለማሳደግ ጥናቱ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የምክክር መድረኩን የመሩት የአስተዳደሩ ምክትል አፈ-ጉባኤ አቶ አብዱልሰላም አህመድ በበኩላቸው ድሬዳዋን ወደ ከፍታዋ የሚመልሰውን ጥናት የሚያከናውኑት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ እየተካሄደ የሚገኘውን ታላላቅ የልማት ሥራ በድሬዳዋም ወንዞች ላይ ለመፈጸም አስተዳደሩ ፣ባለሃብቱና ነዋሪዎች በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡ 

በጥናቱ አተገባበር ወቅት በወንዙ ዳርቻ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ በማመቻቸት የድሬዳዋ የወንዝ ተፋሰሶችና ጎርፍን ወደ ዘላቂ ልማት ለመቀየር ርብርቡ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ጥናቱ የድሬዳዋ ገጽታና ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጥ እንዲሆን የህዝቡን ተሳትፎ ማረጋገጥ፣  ከድሬዳዋ መሪ የዕድገት እቅድና ማስተር ፕላን ጋር መዋሃድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ በከተማ የሚገኙ ሁሉንም ወንዞች ከግምት አስገብቶ መከናወን እንደሚገባም ጠቁመዋል። 

የጥናቱ አስተባባሪ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር አስፋው ከበደ  ድሬዳዋን ለዘመናት ሲያጋጥማት የቆየውን የጎርፍ ስጋትና ችግር በዘላቂነት የሚፈታና ሁለንተናዊ ገጽታዋን የሚለውጥ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም