በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ 32ሺህ ሰዎች ተፈናቀሉ

88

ሰመራ (ኢዜአ) ሐምሌ 29 / 2012 ዓም በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በተለያዩ ወረዳዎች 32 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸዉን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋሰትና ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ገለፀ ።

በአፋር ክልል ክረምቱን ተከትሎ እየጣለ ባለው ዝናብ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በ6 ወረዳዎች 32 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን በፅህፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን ገልፀዋል ።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በክልሉ በአዋሽ ወንዝ ዳርቻ የሚገኙ 7 ወረዳዎች ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት ተጋላጭ ናቸው ።

 ይህን ችግር ለመቅረፍ የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልሉ መንግስት  አካላት ጋር በመቀናጀት የጎርፍ መከላከል ስራዎች ሲያከናውን ቢቆይም የዘንድሮው ክረምት ጠንከር ያለ በመሆኑ በ6 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ አጋጥሟል ።

ጎርፉን ተከትሎ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም 32 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ግምቱ በመጣራት ላይ የሚገኝ ሰብልና እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ።

 እስከ አሁን ድረስ  በአይሳኢታ ወረዳ በጎርጉም ሁለት ቀበሌዎች ለሚገኙ ከ1 ሺህ100 በላይ ሰዎች የፌዴራል መንግስት በሄሊኮፕተር ምግብ የማቅረብ ስራዎች በማከናወን ላይ ነው ።

ከተፈናቃዮች መካከል 17 ሺህ 450 ሰዎች በአይሳኢታ ወረዳ የ5 ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው ።

በተለይም ካለፈው እሁድ ጀምሮ በወረዳው ኮሎዱራና ገለአሊ ቀበሌዎች የአዋሽ ወንዝ ሰብሮ ወደ ቀበሌዎቹ በመግባጋቱ  1ሺህ 126  ሰዎች በውሃ ተከበው ይገኛሉ ብለዋል ።

 ለጊዜው ክልሉ የምግብና ምግብ-ነክ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ በማድረግ የህይወት አድን እርዳታ ለማቅረብ እየሞከረ ቢሆንም ከችግሩ ስፋትና አሳሳቢነት አንፃር የፌዴራል መንግስት እገዛ መጠየቁን አቶ አይዳሂስ ተናግረዋል ።

በመሆኑም ከሰላም ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት ጋር በመተባባር ከዛሬ ጀምሮ በሄሊኮፕተር አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል ።

በውሃ የተከበቡት ሰዎች በሔሊኮፕተርና በሞተር ጀልባ በማውጣት ወደ ሌላ አካባቢዎች ለማስፈር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ከዳይሬክተሩ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

 በአፋር ክልል በታችኛውና መካከለኛው አዋሽ 63 ሺህ ሰዎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ሲሆኑ 44 ሺህ ሰዎች በመፈናቀል ስጋት ላይ የሚገኙ ናቸው ተብሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም