የእናት ጡት በማጥባት ብቻ 14 በመቶ የጨቅላ ህጻናት ሞት መቀነስ ይቻላል

61

ባህርዳር፤ ሃምሌ 29/2012 የእናት ጡት በማጥባት ብቻ 14 በመቶ የሚሆነውን የጨቅላ ህጻናት ሞት መቀነስ የሚቻል በመሆኑ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በትኩረት እንዲሰራ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አሳሰበ።

የጡት ማጥባት ሳምንትን አስመልክቶ “የአገርን ጤና እየጠበቅን የጡት ማጥባትን እንደግፍ”በሚል መሪ ቃል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ።

በቢሮው የእናቶችና ህጻናት ጤና ቡድን መሪ አቶ ስሜነህ ወርቁ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ጡት ማጥባት አንዱና ዋናው የስርዓተ ምግብ ፕሮግራም አካል ተደርጎ እየተሰራ ነው።

የእናት ጡት ለህጻናት እድገትና ጤና የሚያስፈልጉ የምግብ ንጥረ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ በመሆኑ የሚያስገኘውን ጥቅም ለህብረተሰቡ በማስተማር የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

በጡት ማጥባት ላይ ሳይንሱ የሚያዘው አንድ ህጻን ከተወለደ ጊዜ አንስቶ እስከ ስድስት ወር የእናቱን ጡት ብቻ መጥባትና አስከ ሁለት ዓመት ደግሞ ከተጨማሪ ምግብ ጋር መውሰድ አለበት።

በሳንባ ምች፣ በተቅማጥና ሌሎች በሽታዎች የሚከሰት ሞትን ከመቀነስ ባሻገር ለአካላዊና አእምሯዊ እድገት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

 በሌላበኩል ጡት ማጥባት ደም መፍሰስንና የጡት ካንሰርንን በመከላከል እንዲሁም የእርግዝና ጊዜ እንዲራዘም በማድረግ ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይሁን እንጂ በሃገራችን በጡት ማጥባት ያለው ችግር  ከህጻኑ አስተቃቀፍ፣ ከጡት አያያዝና በቀን ቢያንስ ከ10 ጊዜ በላይ ማጥባት ላይ ሳይንሱ ከሚያዘው አንጻር ክፍተት ያለበት ነው ብለዋል።

በዚህም ከቢሮው በተጨማሪ የሚዲያና የኮምዩኒኬሽን ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ህብረተሰቡን በማስተማር የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪ አቶ ፋሲል ታየ በበኩላቸው በሁሉም ሃይማኖቶች የሚገኙ ቅዱሳት መጻህፍት ስለ ህጻናት አስተዳደግ መልካም አስተምህሮዎች አሉዋቸው።

ስለ ህጻናት አስተዳደግ፣ አመጋገብ፣ ጤና አጠባበቅና አያያዝ የተገለጸውን በመጠቀም እስከታች ድረስ ህብረተሰቡን ማስተማርና ሳይንሱ በሚያዘው መሰረት ጡት ማጥባት እንዲተገበር ማድረግ ይቻላል።

በዚህም በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አማካኝነት እስከ ታችኛው አጥቢያ ቤተ እምነቶች ድረስ ሰባኪዎች ትኩረት ሰጥተው ስለ ጡት ማጥባት እንዲያስተምሩ እንደሚያደርጉ አስገንዝበዋል።

የመንግስት ኮምዩኒኬሽን የህትመት አዘጋጅ ባለሙያ የሆኑት አቶ ወለጋ በላይ በበኩላቸው ችግሩ አሳሳቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጡት ማጥባት ሳምንትን አስመልክቶ ብቻ ሳይሆን የእለት ተእለት አጀንዳ አድርጎ ማስተማር አስፈላጊ ነው።

በዚህም ከክልል፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ባለው የተቋሙ መዋቅር ብሮሸር፣ በራሪ ወረቀት፣ መጽሄትና ሌሎች የማስተማሪያ ስልቶችን በመጠቀም ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሰራ  ተናግረዋል።

ከሃምሌ 25 ቀን እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በአገራችን ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረው የጡት ማጥባት ቀን የህብረተሰቡን ግንዛቤ በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እየተከበረ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።