በባሌ ዞን በኮሮና መከላከል የሚታየው መዘናጋት ስጋት አሳድሯል

33

ጎባ (ኢዜአ) ሐምሌ 27/2012 ዓ.ም  በባሌ ዞን በኮሮና መከላከል ረገድ የሚታየውን መዘናጋት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፁ ።

በዞኑ ከጋሰራ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሀሰን መሐመድ በሰጡት አስተያየት አንድንድ ሰው የተናጠል ጥንቃቄ ቢያደርግም አብዛኛው ግን የሽታው የመከላከያ ዘዴዎችን ያለመጠቀም ሁኔታ እንዳለ መታዘባቸውን አመልክተዋል።

በተለይም በገበያ፣ ሆቴልና ትራንስፖርት አጠቃቀም ላይ መጠጋጋትና መጨናነቅ ይስተዋላል ሲሉ ተናግረዋል ።

ይህም የተለመደው ማህበራዊ ህይወት መመለሱን የሚያሳይ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጠው ጠቁመዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል የሚተላለፉ መልዕክቶችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሚስተዋለው መዘናጋት እንዳሰጋቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ አለውያ ሱፊያን ናቸው።

በእሳቸው በኩል ዘወትር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመጠቀም ጭምር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ ቢጥሩም የሌላው መዘናጋት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በአካባቢው ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች መኖራቸው እየታወቀ ርቀትን ያለመጠበቅና ጭንብል ያለመጠቀም ሁኔታ እየተለመደ በመምጣቱ በሽታውን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በጥብቅ እንዲከበር የጠየቁት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ አቶ መስፍን ከበደ ናቸው፡፡

የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ጸሐፊ አቶ ደሰለኝ ቱጁባ እንደሚሉት ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ ህብረተሰቡ ርቀት ያለመጠበቅና ጭንብል ያለመጠቀም ክፍተቶች እንዳሚስተዋሉበት አረጋግጠዋል፡፡

ለዚህም ቀደም ሲል በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ይከናወኑ  የነበሩት የቅስቀሳና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መቀዛቀዝና በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ እንዳሉት ከህዝቡ መዘናጋት የተነሳ በዞኑ በአንድ ቀን እስከ 29 ሰዎች በኮሮና መያዛቻውን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ 

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው ህብረተሰቡን ከበሽታው ለመታደግ የቅስቀሳ ስራዎችን ለማጠናከር በየደረጃው ለሚገኙ የግብረ ኃይሉ አባላት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ህዝቡን ከበሽታው ለመታደግና እየታየ የሚገኘውን ቸልተኝነት ለመቅረፍ የመንግስት መዋቅሮችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የቅስቀሳና ህግን የማስከበር ስራዎች በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በዞኑ በመዘናጋት ምክንያት የኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ በመምጣቱ ማህበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አቶ ዲዳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡