በቤይሩት በተከሰተው ፍንዳታ ቢያንስ 78 ሰዎች ሞተዋል

56

ሐምሌ 29/2012(ኢዜአ) በሊባኖሷ መዲና ቤይሩት በተከሰተው ከባድ ፍንዳታ ቢያንስ 78 ሰዎች ሲሞቱ ከ4ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ።

ፍንዳታው ትናንት ከሰዓት በኋላ 9 ሰዓት አካባቢ የተከሰተ ሲሆን ሙሉ መዲናዋ በፍንዳታው ድምጽ መናወጧን ነው ቢቢሲ የዘገበው።

የአገሪቷ ፕሬዝደንት ማይክል አኑን ፍንዳታው ባጋጠመበት ቦታ ላይ 2 ሺህ 750 ቶን የሚመዝን አሞኒየም ናይትሬት ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስድስት ዓመታት ተከማችቶ ነበር ብለዋል።

ከክስተቱ በኋላም ፕሬዝደንቱ ለዛሬ አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ የጠሩ ሲሆን፤ ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ዘገባው አስታውሷል።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝደንቱ 66 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ፈንድ እንዲለቀቅ አዘዋል።

የሊባኖስ ቀይ መስቀል ሥራ አስኪያጅ ጆርጅ ጄታኒ በበኩላቸው “ከባድ አደጋ ነው የገጠመን። ህይወታቸውን ያጡ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በየቦታው ነው የሚገኙት” ሲሉ ሀዘን በተዋጠ ድምጽ ተናግረዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አሁንም ድረስ ተጎጂዎችን ከፍርስራሽ ስር እያወጡ ሲሆን በዚህም የሞቱ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል።

ትናንት ባለስልጣናት ለፍንዳታው ቀጥተኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ምርመራ እንዲካሄድ ወስነው ነበር።

በፍንዳታው ተጠያቂ የሆኑ አካላት ላይ “ከፍተኛ ቅጣት ይተላለፍባቸዋል” ሲሉ የሊባኖስ የጦር ኃላፊ ተናግረዋል።

የዓለም ምጣኔ ሃብት ፎረም በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ውዝፍ እዳ ውስጥ ከሚገኙ አገራት መካከል ሊባኖስ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትግኝ መረጃው አስታውሷል።