የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አዲስ የመረጃ አስተዳደር ስርአት ይፋ አደረገ

220

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አዲስ የመረጃ አስተዳደር ስርአት ይፋ አደረገ።

የመረጃ አስተዳደር ስርአቱ በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት በጋራ የተዘጋጀ ነው።

ይህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትራንስፖርት አገልግሎት ወጪ ሳይኖርባቸው በአጭር ጊዜና በቀላሉ የእውቅና ፈቃድ፣ የእውቅና እድሳት ፈቃድ እንዲሁም የካምፓስ እና የፕሮግራም ማስፋፊያዎችን ጨምሮ ሁሉንም አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሰጣቸው ፈቃድ መሰረት እየሰሩ ስለመሆናቸው ቁጥጥር ለማድረግና በእያንዳንዱ ተቋም የተመዘገቡ ተማሪዎችን ከመቆጣጠር ጀምሮ ለተለያዩ የትምህርት ተቋማት የጥራት አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ እንደገለጹት፤ የመረጃ አስተዳደር ስርአቱ መንግስት የከፍተኛ ትምህርትን ለማዘመንና ከቴክኖሎጂ ጋር ለማስተሳሰር ከሚያደርገው ጥረት ውስጥ አንዱ አካል ነው።

በአገር ውስጥ አቅም እንደነዚህ አይነት ስራዎችን መተግበር መቻል ለአገሪቱ ኢኮኖሚም ጭምር ተመራጭና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጫ አበረታች ጅማሮ ነው ሲሉም ተናግረዋል።   

ደረጃውን የጠበቀ የመረጃ አስተዳደር ስርአት በመዘርጋት፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን በማዘጋጀት ረገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማርያም በበኩላቸው፤ ዘመናዊ የመረጃ አስተዳደር ስርአት መኖር መረጃዎችን በአግባቡ በማደራጀትና በመተንተን የትምህርት ጥራቱን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና አለው።

እስካሁንም በአገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የተሟላ መረጃ የሚጠቁም አካሄድ እንዳልነበረ አስታውሰዋል።

ይህም በትምህርት ጥራትና አግባብነቱ ላይ ትልቅ ጫና የፈጠረ እና ህገ-ወጥነትንም የፈጠረ አካሄድ ሆኖ እንደቆየም ይናገራሉ።

ይህ ተግባራዊ የሚደረገው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የመረጃ አስተዳደር ስርአትም መረጃዎችን በማደራጀት፣ የተጠቃሚውን ተሳትፎ ለማጎልበትና የትምህርት ጥራቱ እንዲሻሻል ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት የኦንላይን ( የበይነ-መረብ) አሰራር ስርአት የተዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ከቅበላ ጀምሮ እስከ ምረቃ ድረስ የሚያስኬድ መመሪያ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም መመሪያው ተጠናቋል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 250 የሚሆኑ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ሲሆን በእነዚህም ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት እየተከታተሉ ይገኛሉ።