በሃይማኖት ሽፋን ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና የጋራ እሴቶችን ለመሸርሽር የሚደረገውን ጥረት መከላከል ይገባል

89

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) በሃይማኖት ሽፋን ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና የጋራ እሴቶችን ለመሸርሽር የሚደረገውን ጥረት ለመከላከል የሃይማኖት ተቋማት ድርሻቸውን እንዲወጡ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጠየቁ።

ሚኒስትሯ ዛሬ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 12ኛ መደበኛ ጉባኤ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ግጭቶችን በመፍጠር የሕዝቦች አብሮነትን ለመሸርሸር የሚደረገውን ሴራ መከላከል ተቋማቱ ድርሻቸው መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

የሃይማኖት አባቶች አገር ሰላም እንዳትሆን የሚፈልጉ ኃይሎች የእምነት ተቋማትን በማውደም፣የሃይማኖት አባቶችና ተከታዮቻቸው ላይ ጥቃት በማድረስ አገር ለማበጣበጥ የሚያደርጉትን የጽንፈኝነት ተግባር መከላከልና በጋራ መቆም አለባቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ጽንፈኛ የሆኑ አካላት ምዕመናንና የሃይማኖት አባቶች ተስፋ እንዲቆርጡ በማድረግ ሕዝቡን ከመንግሥት ለመነጠል እንደሚሰሩ መታወቅ እንደሚገባውም ወይዘሮ ሙፈሪያት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን በሃይማኖቶች መካከል ለዘመናት በጥልቅ መሠረት ላይ የተገነባ መከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር አኩሪ እሴት እንዳላቸውና ይህንንም በተተኪው ትውልድ ዘንድ ማስቀጠል ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።

የእምነት አባቶች ኅብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በአርአያነት ያከናወኑትን ተግባር ሰላምን በማምጣት እንዲደግሙት ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ከበደ በበኩላቸው ባለፉት ወራት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በጉባኤው የተከናወነው ሥራ ውጤታማ ነበር ብለዋል።

ጉባኤው በቀጣዩ ወር ለሚካሄደው የኮሮና ቫይረስ መከላከል ዘመቻ ከመንግሥት ጎን እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሰባት የሃይማኖት ድርጅቶች በአባልነት አቅፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም