የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጉባኤ ነገ ይጀመራል

75

ድሬዳዋ፣ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የ2012 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ጉባኤውን ነገ እንደሚጀምር የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ ገለጹ።

አፈ ጉባኤዋ በሰጡት መግለጫ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጉባኤው የአስፈጻሚው አካል እና ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ የሆኑ ተቋማት ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

በበጀት ዓመቱ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የተሰሩና በቀጣይ መስተካከል ባሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጉባኤው ይመክራል።

በአስተዳደሩ የስራ አጥነትን ችግር ለመፍታት የተነደፉ ፕሮጀክቶች ፣ የአስፈጻሚው የሥራ ክንውን  እንዲሁም ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ የሆኑ የብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ፣ የዋና ኦዲተር ጽህፈት ቤትና የፍርድ ቤቶች አፈጻጸም እንደሚገመገም  ወይዘሮ ፈጡም አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱ ጉባኤ  የ2013 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ እና ለዕቅድ ማስፈጸሚያ በጀት ፣የተለያዩ ሹመቶች ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡

ጉባኤው  የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን መነቃቃት ወደ ድጋፍ እንዲለወጥ ፣ ኮሮናን ለመከላከል የህዝብ ንቅናቄና የምርመራ ሥራ ስኬታማ እንዲሆን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል፡፡