ተጎጂዎች መንግስት የህግ ማስከበር ስራውን እንዲያጠናክር ጠየቁ

95

ሐረር፣ ሐምሌ 28 /2012 (ኢዜአ)  በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በሁከትና ብጥብጥ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት መንግስት የህግ ማስከበር ስራውን እንዲያጠናክር ጠየቁ ።

የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ አጥፊዎች በህግ ፊት ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል ።

በሐረማያ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሰራዊት ተፈራ በሰጡት አስተያየት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህልፈተ ህይወት ተከትሎ በተነሳው ሁከትና ብጥብጥ ቤት ንብረቴን አጥቻለሁ ብለዋል ።

ድርጊቱን የፈጸሙት አካላት በቁጥጥር ስር ከማዋል አንፃር ክፍተቶች እንደሚታዩ ገልፀው፤ በድርጊቱ የተሳተፉ በሙሉ ለህግ እንዲቀርቡላቸው ጠይቀዋል።

ክፍተቱ በፈጠረው ስጋት አካባቢያቸውን ለቀው በድሬዳዋ ለመኖር መገደዳቸውን ገልፀዋል ።

በሃረማያ ከተማ ባቴ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ስንታየው ተመስገን በበኩላቸው "በአካባቢው ሰኔ 23 ቀን 2012 በተከሰተው ሁከትና ግርግር መኖሪያ ቤታቸው በመቃጠሉ ከዘመድ ቤት ተጠግተው እንደሚገኙ ተናግረዋል ።

የአካባቢው ህብረተሰብና የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉልን ቢሆንም ከመንግስት በኩል ግን እስከ አሁን ድረስ ትኩረት አልተሰጠንም የሚል ቅሬታ አሰምተዋል ።

ህግ የማሰከበር ጅምር ቢኖርም በጥፋቱ የተሳተፉ አካላት ግን ሙሉ በሙሉ እንዳልተያዙ ጠቅሰው፤ ፍትህን የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።

በሁከቱና ግርግሩ በቤት ንብረቱ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት የገለፀው በኮምቦልቻ ወረዳ የመልካ ራፉ ከተማ ነዋሪ ወጣት አዳም እንዳሻው እንዳለው ደግሞ የዞኑም ሆነ የወረዳው አስተዳደር ምንም ዓይነት እገዛ አላደረገለትም ።

በከተማው ችግሩ እንዳይደገምና ያለ ስጋት ለመኖር መንግስት የህግ ማስከበር ስራው አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስተያየቱን ሰጥቷል ።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና  አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ ስለሁኔታው እንደተናገሩት በዞኑ ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብና ፍትህን የማስፈን  ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ቀጥለዋል ።

ከፌዴራል፣ከዞንና ከወረዳ የተውጣጣ የምርመራ ቡድን በማደራጀት በግጭቱ የተሳተፉ 800 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና 400 በሚሆኑት ላይ ማስረጃ ተጠናክሮ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ሁኔታ መመቻቸቱን አስረድተዋል ።

በዞኑ በተከሰተው ሁከትና ግርግር 190 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልፀው፤ በቂ ባይሆንም ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ከቀይ መስቀልና ከዞን አስተዳደር ለተፈናቃዮቹ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

አነስተኛ ጉዳት የደረሰባቸው መኖሪያ ቤቶች እንዲጠገኑ መደረጉን የገለጹት አስተዳዳሪው በተለይ ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ቤቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ከስጋት ተላቆ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ከጸጥታው አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አቶ ሁሴን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም