ፖሊስ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን ገለጸ

84

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በወንጀል ድርጊት በተጠረጠሩት አቶ በቀለ ገርባ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን ገለጸ።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ባለፉት ስምንት ቀናት አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል።

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው ቀርቧል።

መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ባደረገው ማጣራት በተፈጠረው ሁከት በትራንስፖርት ዘርፍ ግምቱ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ጉዳት መድረሱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ማሰባሰቡን ገልጿል።

ሰባት ሽጉጦች ላይ ባደረገው የፎረንሲክ ምርመራ ሁሉም ህጋዊ እንዳልሆኑና የፋብሪካ ቁጥራቸው የተለወጠ መሆኑን እንዲሁም ከተጠርጣሪው ቤት የተገኙ ሁለት ሽጉጦች ህጋዊነት የሌላቸው መሆኑን እንዳረጋገጠ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

”በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት መጣል አለብን” ብለው ባስተላለፉት መልዕክት የተነሳ በተፈጠረ ሁከት በተለያዩ አካባቢዎች የሰው ህይወት ማለፉንና ሰዎች መፈናቀላቸውን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ መኖሪያ ቤት፣ ሆቴል፣ ሱቅ፣ ፋብሪካ፣ የመንግስት ተቋማት እና የሃይማኖት ተቋም መዘረፉንና መቃጠሉን በማስረጃ እንዳረጋገጠ አስረድቷል።

ከተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ውጤት ከመዝገብ ጋር ማያያዙንና የምስክሮች ቃል መስማቱን ተናግሯል።

በተሰማው የምስክርነት ቃል ተጠርጣሪው ከግብረ አበሮቻቸው ጋር የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ከቡራዩ ተመልሶ ወደ ኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት እንዲገባ፣ አስከሬኑ ለ10 ቀናት በአዲስ አበባ እንዲቆይ ተደርጎ የምኒሊክ ሃውልት እንዲፈርስ እንዲሁም ወደ ቤተመንግስት የመግባት ዕቅድ እንዳላቸው ማወቁን ገልጿል።

ፖሊስ ባካሄደው ምርመራ በተጠርጣሪው ላይ ሲያደርግ የነበረውን ማጣራት ማጠናቀቁን ገልጾ፤ ቀዳሚ ምርመራ ለማሰማት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ”መዝገቡ መነሻ ያደረገው የአርቲስት ሃጫሉ አስከሬን እንዲመለስ ማድረግና ስልክ ደውለው ሁከት ቀስቅሰዋል የሚል ነበር” በማለት ገልጸው፤ ሁከት ማስነሳት ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

ደረሰ የተባለው ጉዳት የደንበኛቸውን ድርሻ አመላካች ሆኖ እንዳልቀረበ በመግለጽ ተከራክረዋል።

ቀዳሚ ምርመራ ከመጀመሪያው ጀምሮ መደረግ እንደነበረበት በመግለጽ አሁን ፖሊስ የጠየቀው ቀዳሚ ምርመራ ደንበኛቸውን ከፍርድ ውጪ አስሮ ለማቆየት እንደሆነ በመግለጽ የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪው አቶ በቀለ ገርባ ”እኔ የፓርቲ መሪ እንጂ የሰራዊት መሪ ስላልሆንኩ ህዝብ ያደረሰውን ጉዳት እኔ ላይ መጫን አይገባም” ብለዋል።

”ይሄ መንግስት በምርጫ አልመጣምና ምርጫ ተካሂዶ ህዝብ የመረጠው ፓርቲ ማስተዳደር አለበት በማለት ምርጫው መራዘም የለበትም የሚል አቋም አለኝ” ያሉት ተጠርጣሪው፤ ”በደጋፊዎቼና በእኔ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የተደረገ ነው” ብለዋል።

”ሁከት መቀስቀስ የዋስ መብት አያስከለክልምና የዋስትና መብቴ ሊጠበቅ ይገባል” ሲሉም ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ችሎቱ ማስረጃ መስማት ባለመሆኑ የማስረጃ ምዘና ውስጥ መግባት እንደማያስፈልግ አስረድቷል።

ተጠርጣሪው የቀረበባቸው ማስረጃ የእርስ በርስ ግጭት ማስነሳት እና የሰው ህይወት ያለፈበት በመሆኑና ከ15 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል በመሆኑ ዋስትና ሊፈቀድ እንደማይገባ በመግለጽ ተከራክሯል።

ግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን በማየት ዋስትናን በተመለከተ ውሳኔ ለማሳለፍ ለሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

”የቀዳሚ ምርመራ ማሰማትን በተመለከተ በመዝገቡ ክርክር ማቅረብ ይቻላል” ብሏል።