የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ 50 ሺህ ችግኝ ተተከለ

80

ጎንደር፣ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ 50 ሺህ ሃገረ በቀል ችግኝ መተከሉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ችግኙ የተተከለው በተያዘው የክረምት ወቅት የፓርኩ አዋሳኝ በሆኑ 5 ወረዳዎች በሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ  ነው፡፡

የችግኝ ተከላው ባለፈው ዓመት በእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸውንና የተመናመኑ የፓርኩን የተፈጥሮ ደን መልሶ ለመተካት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ከተተከለው ችግኝ ውስጥ  ለፓርኩ ስነ-ምህዳር መጠበቅ ተስማሚነታቸው በጥናት የተለዩ ወይራ፣ ኮሶና ግራር ይገኙበታል።

በተከናወነው የችግኝ ተከላም 25 ሄክታር መሬት መሸፈኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ከህብረተሰቡ በተጨማሪ በአማራ ክልል የሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎችም ከ5 ሺህ በላይ ችግኝ  በመትከል ለፓርኩ ብዝሃ ሕይወት መጠበቅ አጋርነታቸውን በማሳየት የድርሻቸውን መወጣታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የተተከለው ችግኝ ተገቢው እንክብካቤ ተደርጎለት  ለውጤት እንዲበቃ ፓርኩ ”አፍሪካን ዋይልድ አሶሴሽን” ከተባለ አለም አቀፍ ድርጅት ጋር በደን ክብካቤ ህብረተሰቡን የሚያሳትፍ የምግብ ለስራ ፕሮግራም ስምምነት መፈራረሙንም  አቶ አበባው አውስተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ክረምት በተመሳሳይ ሁኔታ በፓርኩ ክልል ከተተከለው ከ38 ሺህ  በላይ ሀገር በቀል ችግኝ ውስጥ 68 በመቶ ማጽደቅ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

በፓርኩ ደርሶ በነበረ የእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት 573 ሄክታር የጓሳ ሳር እንዲሁም 467 ሄክታር ውጨና የተባለው ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያ በተያዘው ክረምት ሙሉ በሙሉ ማገገሙንም አመልክተዋል፡፡

እንደ ፓርኩ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለጻ ጉዳት የደረሰበት የተፈጥሮ ሀብት በአጭር ጊዜ ማገገም መቻሉ መኖ ፍለጋ ርቀት አካባቢ ተሰደው የነበሩ የፓርኩ የዱር እንስሳት ዳግም ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ አስችሏል፡፡

በደባርቅ ከተማ የሚገኘው የቱሪዝም ልማትና ግብይት ህብረት ስራ ዩንየን ሊቀ-መንበር ቄስ ሞገስ አየነው በበኩላቸው  7 ሺህ የሚሆኑ የዩንየኑ አባላት በፓርኩ ጥበቃና ልማት የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡

የዩንየኑ አባላት በፓርኩ ክልል ችግኝ በመትከልና የዱር እንስሳቱን ከህገ-ወጥ አደን በመከላከል በፓርኩ ጥበቃና ልማት ስራ ተሳታፊና ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት / ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ እንደሆነ ከፓርኩ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡