የአማራ ክልል በችግኝ ተከላው እቅዱን ለማሳካት ተቃርቧል - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል በችግኝ ተከላው እቅዱን ለማሳካት ተቃርቧል

ባህርዳር፣ ሐምሌ 28/2012 ( ኢዜአ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የክረምት ወቅት ለመትከል ከታቀደው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ 87 ነጥብ 5 በመቶ ማከናወን መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እንግዳየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የክረምት ወቅት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ለመትከል ወደ ስራ ተገብቷል ።
በመደበኛውና በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላው ፕሮግራም ለመትከል ከታቀደው ውስጥም እስከ አሁን ድረስ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል።
የችግኝ ተከላው በ154 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መከናወኑን ጠቅሰው፤ በአንድ ጀምበር በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም 190 ሚሊዮን ችግኝ ተተክሏል ።
ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮኑ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች ሲሆኑ ሌሎች ለደን ሃብት ማደግ የጎላ ሚና ያላቸው ችግኞች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ቀሪውን የችግኝ ተከላ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ተክሎ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል።
እየተተከሉ ያሉ ችግኞችን በመንከባከብ የፅድቀት መጠኑን ከ75 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 90 በመቶ ለማሳደግ ከተከላው ጎን ለጎን ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲጠብቅ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በመደበኛም ሆነ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ የተተከሉ ችግኞች በክልሉ አሁን ያለውን 14 ነጥብ 6 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 15 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህም የደን ሽፋኑን ከማሳደግ በተጓዳኝ የአፈር መከላትን በመቀነስ እየተገነባ ያለውን ታላቁ የህዳሴ ግድብና የጣና ኃይቅ በደለል እንዳይሞሉ የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቡገታ ተብሎ በሚጠራው ተፋሰስ የሚገኙ ነዋሪዎች ከ200 ሺህ በላይ ችግኞች ተክለው በጋራ እየተንከባከቡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የኮለል ለቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማረ ላቀ ናቸው።
ቀደም ሲል በዕውቀት ማነስ የወደመውን የተፈጥሮ ሃብት መልሶ ለመተካት በክረምት ወቅት የሚተከሉ ችግኞችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እየጠበቁ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በወረዳው የአባይ ሳንግብ ቀበሌ አርሶ አደር እባሽ መኮነን በበኩላቸው በወል መሬት የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ለማሳደግ የአካባቢው አርሶ አደር በተደራጀ መልኩ አጥሮ የመጠበቅ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በግብርና ባለሙያዎች በሚሰጣቸው ምክረ ሃሳብ መሰረትም በወል መሬቶች የሚተከሉ ችግኞችን ጭምር እንደግል ንብረታቸው እየተንከባከቡ መሆኑን ተናግረዋል ።
በክልሉ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከለው ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ 75 ነጥብ 5 በመቶ ፀድቆ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በተካሄደ የፅድቀት መጠን ጥናት መረጋገጡ ታውቋል።