ኮሮናን ለመከላከል በሚካሄደው ምርመራ ከ17 ሚሊዮን በላይ አባወራና እማወራ ተደራሽ ይሆናሉ

56

አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚካሄደው "የማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ" ዘመቻ ከ17 ሚሊዮን በላይ አባወራና እማወራዎችን ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ለዘመቻው መሳካት ሁሉም እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል። 

"የማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ" ዘመቻ ሰፊ ንቅናቄና ምርመራ ለማከናወን በሚል ባሳለፍነው ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።

ዘመቻው በነሃሴ ወር የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት የሚተገበር ሲሆን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በዘመቻው ማህበረሰቡ የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመግታት ዋነኛ ተዋናይ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለይም የ "መ" ህጎች (መታጠብ፣ መራራቅ፣ መሸፈንና መተሳሰብ) ካለማቋረጥ ዘውትር በተሟላ መልኩ በመተግበር ራስንና ማኅበረሰብን ከቫይረሱ መጠበቅ የዘመቻው ዓላማ ነው ብለዋል።  

በዚህም ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጀምሮ በተለያዩ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሰሩና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጡ ክልከላዎች ላይ ቁጥጥር ይደረጋልም ነው ያሉት።

በዚህም 17 ሚሊዮን አባወራና /እማወራ በዘመቻው ለማዳረስ የታቀደ ሲሆን 200 ሺህ የላብራቶሪ ናሙና ምርመራዎችንም ለማድረግ መታቀዱን ነው የጠቆሙት።  

በተለይም የላብራቶሪ ምርመራዎቹ ቫይረሱ በብዛት የታየባቸው አከባቢዎችና በተለይም ደግሞ በከተሞች አከባቢ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት ዘመቻውን የተሳካ ለማድረግ ከፌደራል እስከ ክልል መዋቅር ባሉ የሚመለከታቸው አደረጃጀቶች የህዝብ ንቅናቄ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ የተጀመረው የህዝብ ንቅናቄ ሥራ ተጠናክሮ አንደሚቀጥልና በተለይም የዘመቻው የላብራቶሪ ምርመራ ሥራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም የአፍና የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች (ማስክ) እና ሌሎች መከላከያ ተግባራት የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በዘመቻው ቫይረሱን ለመከላከል የሚሰሩት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው በቀጣይ ወራቶች እንደሚተገበሩ ጠቅሰዋል።  

ዘመቻውን የተሳካ ለማድረግ የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ለዘመቻው ስኬት ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም