ሙስናና የተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ክርክር ውጤታማነትን የማሳደግ ሥራ ይሰራል

107

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2012 (ኢዜአ)  የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በወንጀል የተገኘ ሀብት፣ ሙስናና የተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ክርክር ውጤታማነት ወደ 98 በመቶ ለማድረስ ማቀዱን አስታወቀ።

የአሥር ዓመት የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ዘርፍ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር የሸሸን ገንዘብ የማስመለስ ጥረቱ እንደሚጠናከርና በትሪሊዮን ብር የሚገመት የአገር ሀብት ወደ ውጭ መሸሹም ተመልክቷል። 

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዕቅድን ያቀረቡት ወይዘሮ አዳነች አበቤ ከ2010 ዓ.ም መጋቢት ወር ወዲህ ዐቃቤ ሕግ ጠንካራ ሥራዎችን መስራቱን ይገልጻሉ።

" የሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዲሁም ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል" ብለዋል።

በዚህም ከ60 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ እየተሻሻለ መሆኑን ጠቁመው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትም የጸረ ሽብር ሕጉ ጭምር መሻሻሉን አስታውሰዋል።

ከሙስና ጋር የተያያዘ ወንጀል የፈጸሙ ወንጀለኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብ የተቻለ ሲሆን የተመዘበረ የህዝብ ሀብት የማስመለስ ስራም መጀመሩን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ በትሪሊዮን ብር የሚገመት የአገር ሀብት ወደውጭ እንዲሸሽ መደረጉን አንድ ገለልተኛ ጥናትን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።

በነዚህ ቅርብ ዓመታት የአገሪቷ ዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝና ጥበቃ መሻሻል ማሳየቱንም በውይይቱ ወቅት ወይዘሮ አዳነች አንስተዋል።

"እነዚህ መልካም የሚባሉ ሥራዎች ቢሰሩም አሁንም የስርዓት አልበኝነት መበራከትና ልማትን የሚፈታተኑ ህገ ወጥ ተግበራት መንሰራፋቱ ትልቅ ችግር ሆኗል" ይላሉ።

የስነምግባር ዝቅጠትም ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ፣ ለአብነትም ሙስናና በሴቶችና ህጻናት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎችን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባሻገር አክራሪ ብሄርተኝነት የፈጠራቸው ብሔር ተኮር ግጭቶች፣ የተደራጀና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መብዛትና ህገ ወጥ ንግድና ያልተገባ ውድድር እየተስተዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በዋናነት መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ መዘጋጀቱንም ነው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ያብራሩት።

እንደ ዋና ግብም ዕቅዱ ወንጀልና የወንጀል ስጋትን መቀነስ፣ ሰብዓዊ መብት ማክበርና ማስከበር እንዲሁም የሕግ ተገዢነት ማሳደግ የሚሉትን አስቀምጧል።

በተለይ ደግሞ ሕጻናትና ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከልና ወንጀለኞችን ፍትሕ ማሰጠት በትኩረት ይሰራል ብለዋል::

"በአሥር ዓመቱ የሕግ ማሻሻያ ሥራዎች ውጤታማነት ማሻሻል፣ የፍትህ አገልግሎት ተገማችነትና ተደራሽነት ማሳደግና የማስፈጸም አቅምን የማሳደግ ሥራዎች ይሰራሉም" ብለዋል ወይዘሮ አዳነች።

በዕቅዱ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የሕግ ባለሙያና ጠበቃው አቶ ደበበ ኃይለገብርኤል በዕቅዱ ውስጥ የሕግ ተርጓሚው ሚና በዝርዝር ቢቀመጥ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

ከምንም በላይ በአግባቡ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ የባለሙያው የሙያ ብቃትና ገለልተኝነት መሆኑንም ነው የገለጹት።

እሳቸው እንደሚሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግን ጨምሮ የፍትህ ዘርፉ ሰዎች በፖለቲካ ታማኝነታቸው አማካኝነት የታጨቁበት ነው።

"በተጨማሪም የግል ሴክተሩ ድጋፍ የሚያገኝበትና የተሻለ ተዋናይ የሚሆንበት መንገድ ቢመቻች ጥሩ ነው " ብለዋል አቶ ደበበ።

በተመሳሳይ የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ የዕቅዱን አጠቃላይ ሁኔታ ያቀረቡት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ ናቸው።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ዘርፉ የተሰላቸና ደካማ ተነሳሽነትን የሚያሳይ የሰው ሀብት ያለበት በመሆኑ ትልቅ ለውጥ ይፈልጋል።

"በአስር ዓመታት ውስጥ ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያለው አገልጋይ መፍጠር እንዲሁም የሰው ሃብት ልማት፣ አስተዳደርና ብቃት የማረጋገጥ ሥራ ይሰራልም" ብለዋል።

በዚሁ መሪ ዕቅድ ላይ ሀሳባቸውን ያቀረቡት ዓለም አቅፍ የልማት ባለሙያዋ ወይዘሮ ማክዳ ጌታቸው ዕቅዱ የመንግስት ሠራተኛው ማበረታቻ ላይ ቢያተኩር የተሻለ ነው ይላሉ።

የማበረታቻ ስርዓቱን ማዘመን፣ የጎንዮሽ ትስስሩን ማጠናከርና የሰው ሃብት አቅም መገንቢያ ተቋማትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ነው ያስረዱት።

በፕላንና ልማት ኮሚሽን አስተባባሪነት የፌዴራል መንግስት ተቋማት የአሥስር ዓመት መሪ የልማት እቅዳቸውን እያስገመገሙ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም