ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ያለባቸው ህሙማን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ጤናማ አኗኗርን ሊከተሉ ይገባል

73

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2012(ኢዜአ) ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተያዙ ህሙማን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ የሚያደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ጤናማ አኗኗርን መከተልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር እንደሚገባቸው ተገለፀ። 

ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ህክምና የሚከታተሉ ህሙማንን የጤና ተቋም ምልልስ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑም ተጠቅሷል።

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኬዝቲም ባለሙያ ዶክተር ሙሴ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ህይወታቸው የሚያልፉ ሰዎች 43 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ነው።

ካንሰር፣ የልብና ደም ቧንቧ በሽታዎች፣ የስኳር ህመም፣ ሥር የሰደዱ የመተንፈሻ አካላትና የኩላሊት በሽታዎች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተገናኘም እነዚህ በሽታዎች ያለባቸው ህሙማን ከበድ ላለ ህመምና ሞት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።

ወረርሽኙ የሚያደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ህሙማኑ በተቻለ መጠን ከቤት ባለመውጣትና የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንዳመላከተው፤ ከመጠን በላይ የወፈሩ ሰዎች በኮቪድ-19 ቢያዙ ለከፍተኛ ጉዳት ይዳረጋሉ፤ እስከ ፅኑ ህክምናና ሞት ደርሳቸዋል ሲል መረጃው ጠቁሟል ።

ዶክተር ሙሴ ጥናቱን ዋቢ በማድረግ እንደተናገሩት፤ በወረርሽኙ ሳቢያ ቤት የሚውሉ ሰዎች ለውፍረት የሚዳረጉ በመሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እንዲያዘወትሩና ጤናማ አመጋገብን መከተል አለባቸው።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር መቀነሱን የተናገሩት ዶክተር ሙሴ፤ የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን  ገልጸዋል።

''ሚኒስቴሩ ባደረገው የጤና ተቋማት ቅኝት የታካሚዎች የጤና ተቋማት ተገልጋይነት መጠን መቀነሱን አረጋግጧል'' ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ህይወት ሰለሞን በበኩላቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሰውነት በሽታ መከላከል አቅም ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ገልጸዋል።

እነዚህ በሽታዎች ህሙማን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የበለጠ ጫና ስለሚደርስባቸው የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ወረርሽኙ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ውስብስብ የጤና ችግር የሌለባቸው ታካሚዎች በስልክ ክትትል እንዲያደርጉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ህሙማኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማዘውተር፣ የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ፣ ትምባሆ ባለማጨስ እንዲሁም አልኮል መጠቀምን በመቀነስ ጤናቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ተገልጿል። 

በተጨማሪም እንደ አካላዊ ጤና ሁሉ የአዕምሮ ጤና መጠበቅ ስለሚገባው ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግና ጭንቀትን በማስወገድ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም