በታችኛው እርከን የሚገኙ አመራሮች ህብረተሰቡን ስለ ኮቪድ-19 በሚገባ አላስተማሩም---ጤና ሚኒስቴር

68

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 27/2012 (ኢዜአ) በታችኛው እርከን የሚገኙ አመራሮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ህብረተሰቡ ለኮቪድ-19 ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ በአግባቡ እንዳላስተማሩት የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኮቪድን አስመልክቶ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲጣስ በቸልተኝነት እያለፉ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ለኢዜአ እንዳሉት በታችኛው እርከን ላይ ያሉ አመራሮች ህብረተሰቡን በማስተባበር ከቫይረሱ እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ዘንግተዋል።

መንግስት ህብረተሰቡንና ባለሀብቱን በማስተባበር ሃብት በማስባስብ፣ የተለያዩ ዕቅዶችና አዋጆችን በማውጣትና የጤና ተቋማትን ዝግጁ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮች ህግን በማስከበርና ዜጎችን በማስተባበር የወጡ አዋጆችን ተፈጻሚ የማድረግ ሥራን በአግባቡ እያከናወኑ አለመሆኑንም ዶክተር ደረጄ አመልክተዋል።

"በዚህ ምክንያትም በአሁኑ ወቅት በክልልም ሆነ በከተማ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው" ብለዋል።

"በከተማ ተዘግተው የነበሩ መጠጥ ቤቶችና ሆቴሎች እየተከፈቱ ነው፤ ስብሰባዎችም እየተበራከቱ ነው።" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳያደርጉ በብዛት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ተናግረዋል።

ማህበራዊ ርቀቶች በሚገባ እየተጠበቁ ባለመሆኑ የቫይረሱ ስርጭት አሁን ካለበት ይበልጥ ይባባስ ይሆናል የሚል ስጋት መኖሩንም ዶክተር ደረጄ አስረድተዋል።

ለኮሮናቫይረስ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች የቫይረሱ ስርጭት መቆሙ በይፋ እስካልተነገረ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያሳሰቡት።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት በአንዳንድ ክልሎች የተለመደው ማህበራዊ እንቅስቃሴ ያለ ምንም ጥንቃቄ በመቀጠሉ የቫይረሱ ስርጭት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው።

"አዲሱን የአኗኗር ዘይቤ ሰዎች እንዲላመዱት ከማድረግ ባለፈ ስለቫይረሱ ስርጭት በሚገባ አውቀው የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሳይገደዱ እንዲተገብሩ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

ይህንን ማድረግ ካልተቻለ የሚወሰደውን የእርምት ርምጃ ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

ታችኛው አመራር ኮቪድ-19 የሚያስከትለውን ጉዳት በሚገባ ተረድቶ በመከላከል ሥራው ለህብረተሰቡ አርአያ መሆን እንዳለበት ዶክተር ደረጄ ተናገረዋል።

በቀጣዩ ሁለት ሳምንታት ከ200 ሺህ በላይ ዜጎችን እንደአገር ለመመርመርም ዕቅድ ተይዞ ወደሥራ ተገብቷል።

ለተጀመረው ለዚህ አገራዊ ንቅናቄ ሁሉም በየክልሉ ዘመቻውን እንዲከፍትና ታች ቀበሌ ድረስ እንዲያስፈጸም ከክልል አመራሮች ብዙ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ18 ሺህ ሲበልጥ የሟቾች ቁጥር 310 መድረሱ ይታወቃል።

ዓለምአቀፍ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተለያዩ የዓለም አገራት የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም