በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጭ ንግድ 164 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

66

አዲስ አበባ (ኢዜአ) 27/2012 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጭ ንግድ 164 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ 

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዘርፉ በበጀት ዓመቱ የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ17 በመቶ ብልጫ አለው።

በ2012 በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጭ ንግድ 226 ሚሊዮን ብር ለማግኘት እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ምክንያት ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰዋል። 

ሆኖም እስከ መጋቢት በነበረው የኤክስፖርት አፈጻጸም ጥሩ የሚባል ቢሆንም ከመጋቢት በኋላ ግን አፈጻጸሙ በአማካይ በ35 በመቶ እንደቀነሰ አበራርተዋል። 

በ2012 በጀት ዓመት ከዘርፉ የወጭ ንግድ 140 ሚሊየን ዶላር እንደነበር የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ ዘንድሮ ግን 17 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 164 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። 

የመላው ዓለም ስጋት ሆኖ የቀጠለው የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያም በተለይ በኢንደስትሪ ፓርኮች እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልፀዋል። 

በተለይ ደግሞ በወጭ ንግድ እንቅስቃሴ፣ የጥሬ እቃ አቅርቦትና ሽያጭ ላይ መቀዛቀዝ ፈጥሯል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ኤክስፖርትን ለማበረታታትና ድርጅቶች ከባድ ኪሳራ እንዳይገጥማቸው በመንግስት በኩል የተለያዩ ርምጃዎች መወሰዳቸውንም አስታውሰዋል።

ኮቪድ- 19 መከሰቱን ተከትሎ የትራንስፖርት ማሻሻያ መደረጉም አንዱ ተጠቃሽ ርምጃ መሆኑን አብራርተዋል። 

የኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑን ተከትሎ ከታዳጊ አገራት እስከ በለፀጉት አገራት ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖው በርትቷል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃ እንዳመለከተው በ2020  ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 ተፅእኖ 5 ነጥብ 1 በመቶ ተገምቷል።

የኮቪድ- 19 ተፅእኖ በዚሁ ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ ላይ የ4 ነጥብ 9 በመቶ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል የተቋሙ መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም