በሰሜን ወሎ ዞን 43 የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኑ

96

ወልድያ ሀምሌ 27/2012 (ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን 43 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን የዞኑ ግብርና ልማት መምሪያ ገለፀ ።

በመምሪያው የሴፍቲኔት መሰረተ ልማት መሀንዲስ አቶ አልይ አራጋው እንደገለጹት ዞኑ ዝናብ አጠርና ተራራማ ስነ ምህዳር የሚበዛበት መሆኑ ለባህላዊ የመስኖ ጠለፋና አነስተኛ ዘመናዊ ግድቦች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል።

በዚህም የአካባቢውን ስነ ምህዳር ከግምት ውስጥ በማስገባት በዘንድሮው ዓመት 43 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ።

ፕሮጀክቶቹ ከመንግስት ከተመደበው 93 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጀት በተጨማሪ በህብረተሰቡ የእውቀትና የጉልበት አስተዋፅኦ ጭምር የተገነቡ ናቸው ተብሏል ።

ፕሮጀክቶቹ 2ሺህ ሔክታር መሬት በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በመስኖ ለማልማት የሚያስችሉ መሆናቸውንም አቶ አልይ ገልፀዋል ።

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ ምንጭ በማጎልበት፣ ወንዝ በመጥለፍ ፣ አነስተኛ ግድብ በመስራት ፣  ኩሬ በመቆፈርና በሞተርና በፔዳል ፓምፕ ከጉድጓድና ከወንዝ ውሀን ስበው እንዲያወጡ በሚያስችል መልኩ የተሰሩ መሆናቸውን ከመሀንዲሱ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል ።

ለመስኖ ግንባታው የዋለው በጀት የተገኘውም ከተከዜ ተፋሰስ፣ ከሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ ከሴፍቲኔትና ከወረዳ መደበኛ በጀት መሆኑን አቶ አልይ ተናግረዋል፡፡

በግንባታውም  በምህንድስና የተመረቁ ስራ አጥ ወጣቶችን በ28 ማህበራት በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ።

አጠቃላይ የግንባታው ሒደት ለ1ሺህ 300 ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል ።

ፕሮጀክቶቹ በዞኑ በመስኖ የሚለማው የመሬት መጠን ወደ 16 ሺህ 428 ሄክታር የሚያሳድገው ሲሆን 10 ሺህ አርሶ አደሮች በአዲስ መልክ የመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ብለዋል ።

በጉባልፍቶ ወረዳ የቀበሌ 14 ነዋሪ አርሶ አደር ቢሆነኝ መልኩ በሰጡት አስተያየት ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ በአካባቢያቸው ያለው ወንዝ እንዲጠለፍላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ጊዜው ደርሶ ዘንድሮ ወንዙን በመጥለፍ ወደ ማሳቸው  ውኃ የሚያስገባ ካናል መገንባቱ የአካባቢውን ህዝብ እንዳስደሰተው ገልጸዋል።

ከ96 ሄክታር በላይ እንደሚያለማ ባለሙያዎች ነግረውናል ያሉት አርሶ አደሩ በዓመት ሶስት ጊዜ በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባሻገር ለገበያ ለማቅረብ እንሰራለን ብለዋል።

የዚሁ ወረዳ የቀበሌ ዘጠኝ ነዋሪና የመስኖ ኮሚቴ ሰብሳቢ አርሶ አደር በሪሁን አስናቀ በበኩላቸው መንግስት በዘመናዊ መስኖ ወንዝ ገድቦ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ካናል በሲሚንቶ ስለሰራላቸው ተደስተዋል።

የመስኖ ግንባታው 78 ሄክታር የሚያለማ በመሆኑ በመጪው ዓመት ቋሚ የመስኖ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል ።

በሰሜን ወሎ ዞን አዲስ የተገነቡት አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ  የመስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደር ቁጥር ወደ 96 ሺህ ከፍ እንደሚያደርገው ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም