በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

77

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 27/2012 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መብራህቶም ኃይሌ ለኢዜአ እንዳሉት የወባ በሽታ የማህበረሰብ ችግር ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው።

በኢትዮጵያ 52 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖር ገልጸው ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።

"በአገሪቱ በሁለት ወቅቶች የወባ ስርጭት ጎልቶ ይስተዋላል" ያሉት አቶ መብራህቶም፣ የክረምት ዝናብን ተከትሎ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ያለው ወቅት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ዝናቡን ተከትሎ ሚያዚያና ግንቦት ወር ላይ የወባ ስርጭቱ በስፋት እደሚስተዋልም እንዲሁ።

አስተባባሪው እንዳሉት በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት በአገሪቱ በወባ በሽታ የተያዙ ሰዎች ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ400 ሺህ ጭማሪ አሳይቷል።

ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ራሱን እንዲከላከል የአልጋ አጎበር ከማሰራጨት ጎን ለጎን በቤት ውስጥ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን አመክተዋል።

በዘንድሮ ዓመት 6 ሚሊዮን አጎበር ለማሰራጨትና 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ታቅዶ ወደስራ መገባቱንም አቶ መብራህቶም ተናግረዋል።

የወባ ምርመራና ህክምናን በስፋት መስጠት ከስትራቴጂው መካከል አንዱ መሆኑን አቶ መብራህቶም ጠቁመው፣ ለዚህም ኀብረተሰቡ ምርመራና የህክምና አገልግሎት በአቅራቢያው እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ የወባ ስርጭት በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በየጊዜው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው።

ህብረተሰቡ የወባ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ መተግበርና በአካባቢው ውሃ የሚያቁሩ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

"በበጀት ዓመቱ በተደረገው የወባ በሽታ ምርመራ የበሽታው ስርጭትም ሆነ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ያሳያል" ሲሉም ገልፀዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት በሚያዚያ ወር ወደጤና ተቋም የመጡ ታካሚዎች ቁጥር ቢቀንስም፣  በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የታየው የታካሚዎች ቁጥር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

በግንቦት እና ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም ወደሕክምና ተቋም የመጡ ሰዎች ቁጥር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ18 እና የ26 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክተዋል።

በሽታው በቀጣይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በ2023 በአገር አቀፍ ደረጃ ወባን ለማጥፋት ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑንና ለዚህም የማስፈፀሚያም ስትራቴጂና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት የወባ በሽታን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ለማጥፋት ታቅዶ እየተሰራ በመሆኑ ኀብረተሰቡ ወባ ጠፍቷል በሚል የሚያሳየውን መዘናጋት እንዲተውና የመከላከል ሥራው አካል እንዲሆን ጥሪ አስተባባሪው አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም