''የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለፍጻሜ እስከሚበቃ ድጋፉ ሊቀጥል ይገባል'' -- ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

69

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 26/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ሳይዘናጉ የግድቡ ግንባታ ለፍጻሜ እስከሚበቃ ድጋፋቸው ሊቀጥል እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

''ድምፃችን ለግድባችን" በሚል መሪ ሃሳብ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ውሃ ሙሌትን በተመለከተ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ በሸራተን አዲስ ሆቴል በነበረው ''ድምጻችን ለህዳሴችን'' መርሃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  ግንባታ ኢትዮጵያዊያን በእልህና በቁጭት በአንድ ላይ የዘመቱበት ነው።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ያሳዩት ትብብርና አንድነት ለአገራቸው ህልውና በጋራ እንደሚቆሙ ያሳዩበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በግንባታው ሂደት እስካሁን ከማህበረሰቡ የተሰባሰበ 13 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መደረጉም ለዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ለህዳሴ ግድብ ደጀን በመሆን ባደረገው ተሳትፎ ግድቡ አሁን ላይ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሊት ስራ በስኬት ተጠናቋል።

ህብረተሰቡ እስካሁን ያደረገው ግድቡ ፍጻሜ እስኪደርስ አሁንም መቀጠል አለበት ብለዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ያለምንም ልዩነት ድጋፋቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ አሁንም ቀጥለዋል ብለዋል።

የዛሬው መርሃ ግብርም የህብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ ከዚህ በኋላም ተጠናከሮ እንዲቀጥል የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በተካሄደው ''ድምፃችን ለግድባችን" መርሃ ግብር ዜጎች በያሉበት ሆነው ደስታቸውንና ድጋፋቸውን በተለያዩ ትእይንቶች አሳይተዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች በክላክስ ደምቀው፣ በሰንደቅ አላማ አሸብርቀው፣ በተለያዩ ጣእመ ዜማዎች ታጅበው አምሽተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም